ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛ አገልግሎት ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ከሁለት ዓመት በፊት መስጠት የጀመረች ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ እና በሌሎች ምክንያቶች ተቋርጦ ቆይቷል፡፡
የጎብኚዎችን ቁጥር ከፍ እንደሚያደርግ የሚገለጸው የመዳረሻ ቮዛ አገልግሎት ከመስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ኢትዮጵያ 190 ሺህ ፓስፖርት ከውጪ ሀገር በማሳተም ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቷን ገልጻለች፡፡
የኢምግሬሽን እና ዝግጅት አገልግሎት ከሙስና ጋር በተያያዘ ሁሉንም ከፍተኛ አመራሮች ከሀላፊነት በማንሳት አዲስ አመራር ከአንድ ወር በፊት ተሾሞለታል።
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ተቋሙን በሀላፊነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው 300 ሺህ ዜጎች ፓስፖርት ለማግኘት ተመዝግበው እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ የተለያዩ ዘመናዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ገልጸው ከዚህ በፊት ለዜጎች እንግልት መነሻ የሖኑ ደላሎች ፣ ህገ ወጥ አሰራር ላይ የተሳተፉ ሰራተኞች እና ሌሎች አካላት በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ በመግለጫቸው ላይ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት አክለውም ፓስፖርት ለመውሰድ ከተመዘገቡ ከስድስት ወር በላይ ለሆናቸው ዜጎች በቅድሚያ ፓስፖርት እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል፡፡