ኢትዮጵያ የ2016 አዲስ ዓመትን ከአምስት ቀናት በኋላ የምታከብር ሲሆን በበዓሉ ዋዜማ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ተዘጋጅተዋል።
የአዲስ ዓመት ዋዜማ ዕለት ከሚዘጋጁ የሙዚቃ ድግሶች መካከል በአዲስ አበባ ሸራተን ሆቴል የተዘጋጀው አንዱ ነበር።
በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ የውጭ ሀገራት እና ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ማስታወቂያዎች በሚዲያዎች በመተላለፍ ላይ ናቸው።
ናይጀሪያዊው ዲቫይን ኢኩቦር ወይም በቅጽል ስሙ ሪማ በመባል የሚታወቀው ድምጻዊ ፣ ከሀገር ውስጥ ደግሞ ልጅ ሚካኤል፣ ኩኩ ሰብስቤ እና ሌሎችን ድምጻዊያን በዚህ የአዲስ ዓመት ኮንሰርት ላይ የሙዚቃ ስራቸውን እንደሚያቀርቡ ተገልጾ ነበር።
ይሁንና ድምጻዊ ሬማ የክርስትና እምነት ላይ ከዚህ በፊት አሹፏል በሚል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በዚህ ኮንሰርት ላይ እንዳይገኙ መልዕክት ማስተላለፏን ተከትሎ በርካቶች ኮንሰርቱን እየተቃወሙ ይገኛሉ።
የዚህ ኮንሰርት ስፖንሰር የነበረው ኮካኮላ ከስፖንሰርነት ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።
በኮንሰርቱ ላይ የሙዚቃ ስራዎቿን ታቀርባለች የተባለችው ድምጻዊ ኩኩ ሰብስቤም ቤተ ክርስቲያኗ ያስተላለፈችውን ጥሪ ተከትሎ ሙዚቃዎቿን እንደማታቀርብ ገልጻለች።
ይህ በዚህ እንዳለ ሌላ የአዲስ ዓመት ኮንሰርት ላይ የሙዚቃ ስራውን ያቀርባል ተብሎ የነበረው ድምጻዊ ንዋይ ደበበ ሀገሬ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና አልዘፍንም ብሏል።
በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
በዚህ ጦርነት በየዕለቱ ንጹሀን ዜጎች እየተገደሉ ነው የተባለ ሲሆን ከቀናት በፊት በሰሜን ሸዋ ዞን ማጀቴ ከተማ በአንድ ቀን በትንሹ 37 ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እያሉ በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸውን ነዋሪዎች ነግረውናል።