ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ኢትዮጵያ ላደረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ተቋማትተወካዮች በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ተሰጠ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስጋኑ አርጋ፤ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ በተለይም በአማራ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ሁኔታ ለተወካዮቹ ገለጻ አድርገዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ የሰብአዊ ሁኔታን ለማሻሻል እና ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን ምግብን ጨምሮ የእርዳታ አቅርቦትን ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው የአማራ ክልል ወደ ቀድሞ ሁኔታው እየተመለሰ መሆኑን በማንሳት፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች አዲስ የክልል አስተዳደር ተቋቁሞ ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶችም ዳግም መጀመራቸውን አስረድተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አያይዘውም፤ አፋጣኝ የሰብአዊ እርዳታ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ያለውን ኹኔታ በተለይም የምግብ አቅርቦትን የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች በፍጥነት እንዲከታተሉ አሳስበዋል ተብሏል።
የሰብዓዊ ድርጅት ተወካዮቹ ጦርነቱ የሰብአዊ ሁኔታውን ይበልጥ እንዳያባብስ የምግብ ዕርዳታውን በጣም ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንደገና ማስጀመር አስፈላጊ መሆኑን መናገራቸው ተገልጿል፡፡
የተመድ ሰብጫዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጽታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከ180 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ማለቱ ይታወሳል፡፡
ከተመድ በተጨማሪም የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት ሁሉም ወገኖች ልዩነቶችን በውይይት እንዲፈቱ እና ድጋፍ እንደሚያደርጉም አሳስበዋል፡፡