ኢትዮጵያ በድንበር ተሻጋሪው አባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች መቋረጡ ይታወሳል።
በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው ይህ የሶስትዮሽ ድርድር በኢትዮጵያ ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል ሲካሄድ ቆይቷል።
በሱዳን እና በኢትዮጵያ የተከሰተው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሶስትዮሽ ድርድር አለመቀጠል እና የግብጽ ተለዋዋጭ አቋም ማሳየት ለድርድሩ አለመሳካት ዋነኞቹ ምክንያቶች ነበሩ።
ከአንድ ወር በፊት በግብጽ ካይሮ በሱዳን ለተከሰተውን ጦርነት እልባት ለመፈለግ በሚል በተካሄደው የጎረቤት ሀገራት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ያቀኑት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) እግረ መንገዳቸውን ከፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር መክረዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከልም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ዋነኛው ሲሆን በሶስት ወራት ውስጥ ዳግም ድርድር ለማድረግ መስማማታቸው ተገልጾ ነበር።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የሶስቱ ሀገራት የህዳሴ ግድብ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ መዲና ካይሮ ተገናኝተዋል።
የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በዛሬው ውይይታቸው በቀጣይ ስለሚደረጉ ድርድሮች፣ የመወያያ አጀንዳዎች፣ እና በሶስቱ ሀገራት ልዩነቶች ዙሪያ እንደሚወያዩ ተገልጿል።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ 84 በመቶ ደርሷል የተባለ ሲሆን የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ሀይል በማመንጨት ላይ ናቸው።
በጣልያኑ ሳሊኒ የግንባታ ተቋራጭ ኩባንያ እየተገነባ ያለው የህዳሴው ግድብ አራተኛው የግድቡ ውሀ ሙሌት ከቀናት በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል።
ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ የሕዳሴ ግድብ ድርድር በግብፅ ካይሮ ተጀመረ
ተቋርጦ የነበረው የሶስትዮሽ የህዳሴ ግድብ ድርድር በዛሬው እለት በግብፅ ካይሮ ተጀምሯል።
የሶስትዮሽ ድርድሩ ከዚህ በፊት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ሲደረግ ቆይቶ ረቂቅ ስምምነት ማዘጋጀት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ከዛ ወዲህ ድርድሩ ሳይካሄድ ቆይቷል።
ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በግብፅ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ከግብፁ ፕሬዝዳንት አብደልፈታህ አልሲሲ ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት የሶስትዮሽ ድርድሩ ዳግም ተጀምሯል።
በዚህም ረቂቅ ስምምነቱ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ድርድር እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
ድርድሩ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት እና የወደፊት የመልማት መብት ባስከበረ መልኩ ለማካሄድም አስፈላጊው ዝግጅት ተከናውኗል።