በኢትዮጵያ ከ4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) ከባለፈው ሕዳር እስከ ሰኔ ወር ድረስ በ3 ሺሕ 300 መጠለያ ጣቢያዎች ሰበሰብኩት ባለው መረጃ፤ በኢትዮጵያ ከ11 ክልሎች ከ4 ነጥብ 38 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል ብሏል፡፡

ከነዚህ ተፈናቃዮች 66 በመቶ የሚሆኑት በግጭት ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ቀሪዎቹ በድርቅ እና በማህበራዊ ችግሮች ምክንያት መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡ሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መገኛ መሆኑ ሲገለጽ፤ ትግራይ፣ አማራ ፣ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች በግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉባቸው አካባቢዎች ናቸው ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ በ10 ክልሎች ተፈናቃዮችን ለመመለስ በተደረገ ጥናት 3 ነጥብ 24 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው መመለስ ይችላሉ በሚል መለየታቸውም ተገልጿል፡፡

ተቋሙ አክሎም በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈናቃዮች የተመለሱባቸው ክልሎችም አማራ፣ ትግራይ እና አፋር መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በአማራ 44 በመቶ፣ በትግራይ 39 በመቶ እና በአፋር ስድስት በመቶ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው ተመልሰዋል ተብሏል፡፡

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ከዚህ በተጨማሪ በጸጥታ ችግሮች እንዲሁም በመንገድ እጦት የተነሳ ጥናት ያላደረገባቸው የተፈናቃይ መገኛ ቦታዎች እንዳሉ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ግጭት፣ ድርቅ እና ጎርፍ በመሳሰሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተመድ ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡


ኢትዮጵያ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በተጨማሪ የሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ዜጎችን በሀገሯ ያስጠለለች ሲሆን በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎች በኢትዮጵያ ተጠልለዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *