ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኛትን የባቡር መስመር በ14 ቢሊዮን ዶላር ልትዘረጋ መሆኑን አስታውቃለች፡፡
ኬንያ የምትዘረጋው ይህ ፈጣን የባቡር መስመር በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሲሆን፤ መነሻውን ከህንድ ውቅያኖስ ላሙ ወደብ በማድረግ ኢትዮጵያን እና ደቡብ ሱዳንን እንደሚያገናኝ ብሉምበርግ ዘግቧል።
በዓይነቱ ልዩ ነው የተባለው ይህ የባቡር መስመር በፈረንጆቹ 2025 ሥራ እንደሚጀመር እና 3 ሺሕ ከሎ ሜትር እንደሚረዝም ታውቋል፡፡
የባቡር መስመሩ መነሻውን ከህንድ ውቅያኖስ አድርጎ፣ በኬንያዋ ማዕከላዊ ከተማ ኦሲዮሎን በኩል፣ ናይሮቢን እና አዲስ አበባን በማገናኘት የመጨረሻም መዳረሻውን ደቡብ ሱዳን ጁባ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡
ይህ ፈጣን የባቡር መስመር “ኢትዮጵያ በአሰብ እና ምጽዋ እንዲሁም ጅቡቲ ወደቦች ላይ ያላትን ጥገኝነት የሚቀንስ ነው” የተባለ ሲሆን፤ ሌሎች በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዳሉትም ተገልጿል፡፡
በዚሁ ፈጣን የባቡር መስመር ዝርጋታ አማካኝነት ደቡብ ሱዳን ኹለተኛ ወደብ እንደሚኖራትም ተመላክቷል።
የባቡር መስመር ዝርጋታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠጥ በሚጀምርበት ወቅት ከላሙ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የላሙ ወደብን ለማልማት እና ለመጠቀም በ2001 ዓ.ም በኬንያ ፕሬዝዳንት፣ ሞ ኪባኪ፣ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት አማካኝነት ስምምነት ተፈራርመዋ፡፡
ኬንያ ይህን ፕሮጀክት በማልማት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን እንዲጠቀሙበት ፍላጎት ያላት ቢሆንም ኢትዮጵያ እስካሁን ፍላጎት እንዳልነበራት ተገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ኢትዮጵያ ተጨማሪ የገቢ ወጪ ንግድ አማራጭ ወደብ እንዲኖራት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆን የላሙ ወደብን አንዱ አማራጭ አድርጎ ለመጠቀም መወሰኑ ተገልጿል፡፡
ይህ ተከትሎም ኬንያ ከላሙ ወደብ በሞያሌ አድርጎ አዲስ አበባ የሚደርስ የባቡር መሰረተ ልማት ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡