የኢትዮጵያ አየር መንገድ 26 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግ እና ኤርባስ ጋር ድርድር ጀመረ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ካዘዛቸው 26 አውሮፕላኖች ውስጥ ስምንቱን በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚረከብ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አየር መንገዱ ተጨማሪ 26 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ከቦይንግና ከኤርባስ ከተሰኙ ግዙፍ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች ድርድር በማድረግ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አየር መንገድ በቀጣዮቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ስምንት አውሮፕላኖችን እንደሚረከብ አስታውቋል።

ከተገዙት አውሮፕላኖች መካከል አየር መንገዱ ስምንት የመንገደኛ አውሮፕላኖች በጥቂት ወራት ውስጥ እንደሚረከብም ነው የገለጹት።

ቀሪዎቹ የመንገደኞች አውሮፕላኖች በቀጣይ ጊዜያት እንደሚገቡ ገልጸው፤ አየር መንገዱ ሌሎች ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለማስገባት እቅድ እንዳለው ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም አየር መንገዱ በሰኔ ወር ከቦይንግ ኩባንያ ሊረከባቸው ግዥ የፈጸመባቸው ኹለት አውሮፕላኖችም በመጪው መስከረምና ጥቅምት ወራት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አየር መንገዱ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ የመዳረሻ ሥፍራዎችን ከማስፋት አኳያ በቀጣይ ጥቅምትና ሕዳር ስድስት የበረራ መዳረሻዎች እንደሚጨምር ተናግረዋል።

እነዚህ የበረራ መዳረሻዎች በአብዛኛው የአውሮፓ አገራትን እንዲሁም አንድ አፍሪካ አገርን ትኩረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም፤ ስፔን ማድሪድ፣ እንግሊዝ ለንደን-ጋትዊክ፣ ኔዘርላንስ አምስተርዳም፣ ቬትናም ሃኖይና ማዕከላዊ አፍሪካ ባንጓይ የአየር መንገዱ አዳዲስ መዳረሻዎች እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በተያዘው በጀት ዓመት ገቢውን በ22 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ለዚህም ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የአውሮፕላን ቁጥር መጨመርና ከበረራ መዳረሻውን ማስፋት በተጨማሪ የመሰረተ ልማት ማስፋፊና የደንበኞች አገልግሎት የማሻሻል ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱን በሌሎችም በርካታ ዘርፎች የሪፎርም ሥራ በማጠናከር የታቀደውን እድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም መስፍን ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአሁኑ ወቅት 145 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን፤ 134 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ መዳረሻዎች አሉት።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *