ሰላምዊት ዳዊት የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ሀላፊ ሆነው ተሾሙ

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ሰላማዊት ዳዊትን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሀላፊ አድርገው ሾሙ።

የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ሶስት ከፍተኛ አመራሮች ከሀላፊነት መነሳታቸው ተገልጿል።

ፓስፖርት እና መሰል የዜግነት አገልግሎቶችን ለመስጠት የተቋቋመው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋም ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ላለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ብሩህተስፋ ሙልጌታን፣ በምክትል ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ፍራኦል ጣፋ እና ታምሩ ግንበቶን ከኅላፊነት አንስተዋል።

የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙንኬሽን ሀላፊ ወይዘሮ ማስታዋል ገዳ ለአልዓይን እንዳሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ከሰኔ 12 ቀን 2015 ዓም ጀምሮ ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሶናል ብለዋል።

እንዲሁም አቶ ጎሳ ደምሴ እና ቢቂላ መዝገቡ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንደተሾሙ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተፈረመ ደብዳቤ ደርሶናልም ብለዋል።

ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት አዲሱን ሹመት ከመቀበላቸው በፊት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ሀላፊ ሆነውም አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም በያዝነው ዓመት አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት አልያም ለማሳደስ የፈለጉ ዜጎች እየተጉላሉ መሆኑን አልዐይን ከሁለት ሳምንት በፊት ያነጋገራቸው አገልግሎት ፈላጊ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል።

አገልግሎት ለማግኘት በሚልም በኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ያገኘናቸው ተገልግጋዮች እንዳሉን ከሆነ የፓስፖርት ጉዳይ የዜጎች መሰረታዊ መብት ቢሆንም ፓስፖርት ቅንጦት ሆኖብናል ብለዋል።

ፓስፖርት ማግኘት ለዜጎች ቀላሉ ነገር መሆን ነበረበት ያለን ደግሞ ሌላኛው አገልግሎት ፈልጊ ሲሆን ዜጎች ፓስፖርት ለማግኘት ከተቀመጡ ህጋዊ አሰራሮች ይልቅ አቋራጭ እና ህገወጥ መንገዶችን እንዲከተሉ ይበረታታሉም ብሎናል።

የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በበኩሉ አሁን ላይ ፓስፖርት እየሰጠ ያለው ለህክምና ወደ ውጪ ሀገር ለሚሄዱ፣ ስኮላርሽፕ እድል ላገኙ፣ ድቪ ሎተሪ ለደረሳቸው እና ለመንግስታዊ አገልግሎት ወደ ውጪ ሀገራት ለሚሄዱ ሰራተኞች እና አመራሮች ብቻ መሆኑን ገልጿል።

ፖስፖርት ለሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ ፓስፖርቱን ለምን መስጠት አልተቻለም? በሚል ላቀረብነው ጥያቄም ኢትዮጵያ የፓስፓርት ህትመትን በውጭ ሀገራት እንደምታካሂድ ነገር ግን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ህትመቱን ያካሂድ የነበረው ድርጅት ላይ ጫና በመፈጠሩ የፓስፖርት እጥረት እንደተፈጠረም ገልጿል።

በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በረራ በመቀነሱ የፓስፖርት ህትመት ፍላጎት ቀንሶ ነበር ያለን ድርጅቱ ነገሮች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ የፓስፖርት ህትመት ፈላጊ ሀገራት ቁጥር በመብዛቱ ኢትዮጵያ እንዲታተምላት ያዘዘችው ፓስፖርት በተፈለገው መጠን እና ጊዜ ውስጥ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ አይደለምም ብሏል።

እጃችን ላይ ያለውን የተወሰነ ፓስፖርት ለተመረጡ አስቸኳይ አገልግሎቶች እየሰጠን ነው የሚለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ክፍያ ፈጽመው፣ አሻራ ሰጥተው እና አስፈላጊውን መስፈርት ሁሉ አሟልተው ፓስፖርታቸውን ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች እንዳሉ አስታውቋል።

ፍላጎቱን ማሟላት የሚያስችል ፓስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ በቅርቡ እናስገባለን ያለው ድርጅቱ ከመስከረም 2016 ጀምሮም የፓስፖርት ጠያቂ ዜጎችን ፍላጎት እናሟላለን ሲልም ምላሽ ሰጥቶም ነበር።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *