ኢትዮጵያ ከያዝነው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ባሉት አምስት ወራት በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ገደብ ጥላለች።
ኢትዮጵያ የኢንተርኔት እገዳውን የጣለችው በቲክቶክ፣ ቴሌግራም፣ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ነው።
በኢንተርኔት እገዳው ምክንያትም ኢትዮጵያ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ ማጣቷን የመብቶችና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ገልጿል፡፡
“ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶችን ተከትሎ፤ ከ2008 ወዲህ የበይነመረብ ግንኙነትን ማቋረጥ በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣ ችግር ነው” ያለው ማዕከሉ፤ የበይነመረብ ግንኙነት መቋረጡ የዴሞክራሲና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት ጸር መሆኑን አመላክቷል፡፡
መንግሥት ዋና ዋና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በኢትዮጵያ እንዳይጎበኙ እገዳ መጣሉ ሕጋዊ መሰረት የሌለው ነው ሲልም ገልጿል፡፡
የበይነመረብ ግንኙነት መቋረጥ ትኩረት ሊያገኝ ባለመቻሉም የሰብዓዊ መብቶች እሴቶችን እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ የተጠበቁ የሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶችን እየገፈፈ ነውም ተብላል።
በዚህም በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ በተጣለው ገደብ ከ140 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር በላይ የኢኮኖሚ እንዲሁም፤ 27 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ቀጥታ የምርት ገበያ ኪሳራ ማድረሱን እና 2 ሺሕ 372 ሰዎች ሥራ እጥ እንዲሆኑ ማድረጉንም ማዕከሉ በሪፖርቱ አስታውቋል።
የበይነመረብ ግንኙነት መቋረጥ ዘመናዊ ንግዶችን በማደናቀፍ ኢኮኖሚው በየጊዜው በሚሊዮን ዶላሮች እንዲያጣ እንደሚያደረገውና፤ የምርጫ ተዓማኒነትን የሚያጎድል መሆኑን ማዕከሉ ገልጿል።
ማዕከሉ በኢትዮጵያ የበይነመረብ ግንኙነትን የማቋረጥ ተግባር “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና መረጃ የማግኘት መብቶችን” እያደናቀፈ መሆኑን ገልጾ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ይህንን የመንግሥትን ሕጋዊ መሠረት የሌለው ተግባር በፍርድ ቤት ሊሞግቱት እንደሚገባም አሳስቧል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ የበይነመረብ ግንኙነት ማቋረጥን መቃወም አለበት ያለው ማዕከሉ፤ በኢንተርኔት ገደብ የሚጣለው የመረጃ የማግኘት ማዕቀብ እንዲነሳ የራሱን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ መንግሥት በኢነርኔት ላይ የጣለው ገደብ ዜጎች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ አክሎም መንግሥት ከአምስት ወር በፊት በተወሰኑ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የጣለውን የኢንተርኔት ገደብ እንዲያነሳም ጠይቋል።