በኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ቁልፍ ሰብረው እየገቡ መሆኑ ተገለጸ

በሸገር ከተማ አስተዳደር በሚገኘው ኮዬ ፈጬ ኮንዶሚኒየም ለባለእድለኞች በተላለፉ ቤቶች ውስጥ ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ቁልፍ ሰብረው በመግባት ወረራ እየፈጸሙ መሆኑን የኮንዶሚኒየሙ ሕጋዊ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በኮንዶሚኒየሙ የእጣ እድለኞች ሆነው ለባለቤቶች ቁልፍ ተላለፈው፤ ነገር ግን ተቆልፈው በተቀመጡ ቤቶች እና እስካሁን ለባለእድለኞች ባልተላለፉ ቤቶች ላይ የማይታወቁ ሰዎች ወረራ እየፈጸሙ ነው ተብሏል።

ይህን ድርጊት ለመከላከል ጥረት በሚያደርጉ የኮንዶሚኒየም የጥበቃ ሠራተኞች ላይም ዛቻ እና ማስፈራሪያ በማድረስ ሰዎቹ በኃይል እየገቡ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ዘግቧል፡፡

ነዋሪዎቹ አክለውም፤ “ተዘግቶ የተቀመጠን ቤት በኃይል ሰብረው ገብተው ወረራ ሲፈጽሙ አንድም የመንግሥት አካል ሊያሰቆማቸው የሞከረ የለም፡፡” ሲሉ ተደምጠዋል።

ከመጋቢት 2015 ጀመሮ በኮንዶሚኒየሞቹ ላይ ከፍተኛ ወረራ እየተካሄደ መሆኑን በመጠቆምም፤ “ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ብናቀርብም መፍትሔ ሊገኝ አልቻለም፡፡” ብለዋል፡፡

በዚህም ወደ ኮንዶሚኒየሞቹ የሚገቡና የሚወጡ ሰዎችን ማንነት ማወቅ ባለመቻሉ ሕጋዊ ነዋሪዎችን ስጋት ውስጥ ከቷል ነው የተባለው።

አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኮንዶሚኒየሙ የጥበቃ ሠራተኛ በበኩላቸው፤ ማንነታቸውን መናገር የማይፈለጉ ሰዎች የተዘጉ ቤቶችን ቁልፍ በኃይል ሰብረው በመግባት እየኖሩበት ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አክለውም ችግሩ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን በመጠቆም፤ ድርጊቱን ማሰቆም አለመቻሉን ገልጸዋል።

“ኮንዶሚንየሙን እንድንጠብቅ የተቀጠርነው የጥበቃ ሠራተኞች ደሞዛችን ከተቋረጠ ኹለት ወር በማለፉና ይህን ተከትሎም የጥበቃ ሥራችንን በአግባቡ እየሰራን ባለመሆኑ ሕገወጥ ድርጊቱ ተባብሶ ቀጥሏል” ሲሉም አክለዋል።

ኮንዶሚኒየሙ የተሰራው ለልማት ተነሽ ለሆኑ በቀበሌ ቤት ለሚኖሩ ሰዎች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ቤቶቹ የመንገድ እና የመብራት መሰረተ ልማት እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቁ መሆናቸውን ተከትሎ ባለእድለኞች ቤታቸውን ቆለፈው እንዳስቀመጡት ተጠቅሷል።

የቤቶቹ መሰረተ ልማቶች እስኪሟሉ ድረስ በሚል ተዘግተው ከተቀመጡት በተጨማሪ ለባለእድለኞች ያልተላለፉ በርካታ ቤቶች መኖራቸው ማንነታቸው የማይታወቁ ሰዎች ወረራውን እንዲፈጽሙ አመች ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ነው የተባለው።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡ የተደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ እንዳልተሳካ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *