ኢትዮጵያ ለአምስት የውጭ አገር ባንኮች ፍቃድ እንደምትሰጥ ገለጸች

አምስት የውጭ አገር ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ገብተው አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸው ፈቃድ እንደሚሰጣቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

አገር በቀል ባንኮች ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ እና ቀድሞ የነበራቸውን ስትራቴጂ መከለስ እንዳለባቸውም ባንኩ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የገንዘብ ተቋማት ዘርፍ ምክትል ገዥ አቶ ሠለሞን ደስታ እንዳሉት የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማትን ከማጠናከር ጎን ለጎንም የውጭ ባንኮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው።

‹‹ሥራውን አሁን እያጠናቀቅን ነው። አዋጁን የመከለስ ሥራውንም እያጠናቀቅን ነው:: ከለጋሾች አንዳንድ ግብዓቶችን እየጠየቅን ነው። በወራት ዕድሜ ለህዝብ እንደራሴዎች ይቀርባል:: ስለዚህ ስራው እየተፋጠነ ነው” ብለዋል አቶ ሠለሞን።

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ሠለሞን ገልጸዋል።

እንደ ምክትል ገዥው ገለጻ፤ የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ባንኮችን ከገበያ እንዳያስወጧቸው የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ሊሰሩ ይገባል፤ለዚህም የተቀመጠ አሰራር መኖሩን አመልክተዋል።

ተቋማቱ ከመደበኛ በጀታቸው ሁለት ከመቶ የሚሆነውን ለአቅም ግንባታ እንዲያውሉትና ይህም ለባንኮች ከረጅም ዓመታት በፊት የተላለፈ መሆኑን፣ አሁንም ድረስ በዚሁ አግባብ ክትትል እንደሚደረግ አቶ ሠለሞን አስረድተዋል።

አሁን ቀድሞ እንደተለመደው መሄድ አይቻልም ያሉት አቶ ሠለሞን፣ ሪፎርም ከተደረገ ወዲህ ብዙ አዳዲስ ነገሮች አሉ፤ በጀት ተመድቦም በሰፊው መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

“በተለይም ማን ከማን ጋር መሥራት አለበት፤ ማን ከማን ጋር ቢዋሃድ ያዋጣል የሚለውን ከአሁኑ ማሰብ ይገባል:: ከውጭ ከሚመጡ ተቋማትም ጋር እንዴት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ከወዲሁ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፤ ካፒታል፣ እውቀት እና ቴክኖሎጂ እንዴት መጋራት እንደሚቻልም ባንኮቹ ከወዲሁ ሊያጤኑት ይገባል:: በተጨማሪም ሌሎች ባንኮችን ሄደው መጎብኘት አለባቸው” ሲሉም መናገራቸውን የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዘግቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *