የመንግሥት ዓመታዊ በጀት ጉድለት የ281 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳየ

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ የመንግሥት በጀት የ281 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንደገጠመው የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴ አስታውቀዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 በጀት ዓመት የመንግሥት በጀት 801.65 ቢሊዮን ብር እንዲሆን፤ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ምክር ቤቱ የቀረበውን የበጀት ረቂቅ እየገመገመ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት፤ መንግሥት ለ2016 ካረቀቀው አጠቃላይ በጀት ውስጥ የ281 ቢሊዮን ብር ጉድለት ማጋጠሙን ጠቁመዋል፡፡

የዓመቱ የበጀት ጉድለት በመጠናቀቅ ላይ ከሚገኘው የ2015 በጀት ዓመት የበጀት ጉድለት 50 ቢሊዮን ብር ገደማ ሆኗል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 786 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ የበጀት ጉድለቱ 231 ቢሊዮን ብር መሆኑን ሚኒስትሩ የዓመቱን በጀቱ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው በጀት ዓመት ከልማት አጋሮች የሚገኘው የልማት ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ “በበጀት ድጋፍ መልክ ይገኛል ተብሎ የተያዘው ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ሳይገኝ ቀርቷል።” ብለዋል፡፡

የ2015 በጀት ዓመት የመንግሥት ወጪ መጨመሩን ተከትሎ፤ መንግሥት የገጠመውን የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን መገደዱም ተጠቁሟል፡፡

የዓመቱን የበጀት ጉድለት የውጭ ብድር እንደ አማራጭ ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ ለበጀት ጉድለት እንደ አማራጭ ተይዞ ስለነበረው የ7 ቢሊዮን ብር የውጭ ብድር ሚኒስትሩ ያሉት ነገር የለም፡፡

በተመሳሳይ 2016 የበጀት ጉድለት ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ብድር እንደሚሞላ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ከአጠቃላይ የበጀት ጉድለቱ ውስጥ 242 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ብድር፣ ቀሪው 39 ቢሊዮን ብር ከውጭ ብድር እንደሚሸፈን ተናግረዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *