የአውሮፓ ህብረት በአማራ እና ኦሮሚያ ያለው ውጥረት እንደሚያሳስበው ገለጸ

የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮ ነጋሪ በላከው መግለጫ እንደገለጸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ወደ ነበረበት እንዲመለስ መወሰኑን ገልጿል፡፡

የህብረቱ አባል ሀገራት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ስብሰባ ህብረቱ በሰሜን ኢትዮጵያ ባጋጠመው ጦርነት ምክንያት ሻክሮ የነበረው ግንኙነት መሻሻሉን አስታውቋል፡፡

በተለይም የፌደራል መንግስት እና ህወሃት በአፍሪካ ህብረት አደራዳረነት የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን እንደተቀበለው ህብረቱ ገልጿል፡፡

በዚህም ምክንያት የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ መወሰኑን አስታወቋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸው ህብረቱ የተጀመረው የሽግግር ፍትህ እና ብሄራዊ ምክክር እቅድ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ አደርጋለሁም ብሏል፡፡

ይሁንና በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ያለው የፖለቲካ መካረር የጸጥታ ችግሮች መባባስ እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳሳሰበው ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ህዝብን ማዕከል ያደረገ እና አሳታፊ ውይይት እንዲያደርግ ያሳሰበው የአውሮፓ ህብረት ለግጭት አፋታት ስራዎች እና ሌሎች የኢትዮጵያ እቅዶች ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የአውሮፓ ህብረት ያወጣቸውን መግለጫዎች እንደሚቀበል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መግለጹ ይታወሳል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *