የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት አሳየ

የኢትዮጵያ የዘጠኝ ወራት የወጪ ንግድ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉድለት አሳየ።

የንግድ እና ቀጠናዊ ውህደት ሚንስቴር እንደገለጸው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር።

ይሁንና የተገኘው ገቢ ግን በአንድ ቢሊዮን ዶላር ቀንሶ 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል ተብሏል።

ለገቢው መቀነስ የጸጥታ ችግሮች፣ ህገወጥ ንግድ፣ የዓለም ንግድ መቀዛቀዝ እና የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በምክንያትነት ተጠቅሰዋል።

ከተገኘው ገቢ ውስጥም ግብርና የ77 በመቶ ድርሻ ሲያዝ ቀሪው ማዕድን፣ ኢንዱስትሪ እና ኤሌክትሪክ ሽያጭ እንደሆኑ ሚንስቴሩ ገልጿል

ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነት ውስጥ የቆየችው ኢትዮጵያ የወጪ ንግዷ ተዳክሞ የቆየ ሲሆን በአሜሪካ የተጣለባት ማዕቀብ፣ ህገወጥ የማዕድን ገበያ መስፋፋት ለወጪ ንግዱ ዋነኛ ችግሮች ነበር።

አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ኢትዮጵያን ከአግዋ እድል የሰረዘቻት ሲሆን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ አሜሪካ ገበያ ይላኩ የነበሩ ምርቶች የገበያ እድል አጥተው አምራች ኢንዱስትሪዎች ኢትዮጵያን ለቀው ተሰደዋል።

የአሜሪካንን ማዕቀብ ተከትሎም በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ኩባንያዎች ሲዘጉ ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ዜጎችም ለስራ አጥነት ተጋልጠዋል።

ይሁንና ባሳለፍነው ህዳር በደቡብ አፍሪካ በፌደራል መንግሥት እና ህወሀት መካከል በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ የንግድ እንቅስቃሴዎች እየተነቃቁ መጥተዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እየጨመረ መጥቷል የተባለ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ቆመው የነበሩ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ስራዎች ዳግም ወደ ስራ እየገቡ እንደሆነ ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *