የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ የክልል ልዩ ሀይሎችን በሚመለከት በተፈጠሩ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
ተቋሙ እንዳለው የልዩ ሀይሎችን መልሶ የማደራጀትን ውሳኔ ትግበራ በውይይትና የሰዎችን ሰብአዊ መብቶች አደጋ ላይ በማይጥል ሁኔታ ሊከውን ይገባል ሲል አሳስቧል
ኢሰመኮ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራልና በክልል መደበኛ የጸጥታ ኃይሎች ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መልሶ ለማደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔና ትግበራ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ተቃውሞዎች፣ የጸጥታ መደፍረስ እና በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሱ ግጭቶችንና ጉዳቶችን በተመለከተ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
ኮሚሽኑ በተለይም በቆቦ፣ በባሕር ዳር፣ በወረታ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን እና በመራዊ የተቃውሞ ሰልፎች፣ መንገድ መዘጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች መካከል ፍጥጫዎች የተከሰቱ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎችና ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችን ጨምሮ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት አስከትሏልም ብሏል።
በሌላ በኩል በእነዚህ ከተሞችና ሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠረው ውጥረት፣ አለመረጋጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እና የእንቅስቃሴ እገዳዎች ምክንያት በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ሥራ ላይ እንቅፋት እንደፈጠረም ኮሚሽኑ ገልጿል።
አጠቃላይ ችግሩና የጸጥታው ሁኔታ አስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋት በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በምክክርና በመግባባት እንዲፈቱ ኮሚሽኑ አሳስቧል።
ኮሚሽኑ አክሎም በተለይም አጠቃላይ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታው የፈጠረውን ሥጋትና የአለመተማመን ስሜት ከግምት በማስገባት መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔውን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ለሚመለከታቸው ሁሉ በትዕግሥትና በጽሞና የሚያስረዳበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባልም ብሏል።
የጸጥታ አካላት ያልተመጣጠነ እና ሕይወት የሚያጠፋ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ መንግሥት ስለደረሰው ጉዳት ሁሉ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲያረጋግጥ እንዲሁም ሁሉም ሰው ሐሳቡን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲገልጽ ኢሰመኮ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።
ኢሰመኮ ከመደበኛው የክትትል እና ምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በማነጋገር እና ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት የተፈጠረው ችግር በውይይት እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል።