መንግሥት በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ በድጋሚ ተጠየቀ

የኢትዮጵየ መንግሥት ፌስቡክ እና ዩቲዩብን ጨምሮ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የጣለውን ገደብ እንዲያነሳ የጠየቀው ዓለም አቀፉ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ነው፡፡ 

አምነስቲ የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮቹ ከተገደቡ አንድ ወር እንደሞላቸው ዛሬ ሐሙስ የካቲት 30፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡ 

በጉዳዩ ላይ የተናገሩት የአምነስቲ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ፍላቪያ ምዋንጎቪ፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ እና ዩቲዩብን ማኅበረሰቡ እንዳይጠቀም ገደብ ከጣሉ አንድ ወር እንደሞላቸው አስታውሰው፤ ይህም ‹‹የዜጎችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽና መረጃን የማግኘት መብቶችን በግልጽ የሚጥስ ነው›› ብለዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ አምነስቲ የጠቀሳቸው የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ገደበ የተጣለባቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረ ክስተት ተከትሎ ውጥረት በመስፈኑ ነበር፡፡ 

የመብቶች ተሟጋቹ በመግለጫው በቤተ ክርስቲያኗ በተፈጠረው ክስተት መንግሥት ጣልቃ በመግባት ወረራዎች፣ እስሮች እና ግድያዎች ተፈጽመዋል በሚል ሰልፍ ተጠርቶ የእንደነበር በመግለጽ፤ የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮቹ ገደብም ከዚህ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ በተወሰኑ የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተጣለው እገዳ ምክንያት ተገልጋዮች የትስስር መድረኮቹን ለማግኘት ቪፒኤን የተባሉትን መተግበሪያዎች ለመጠቀም የተገደዱ ሲሆን፣ እገዳውን ተከትሎም እነዚህን ዕቀባ የተጣለባቸውን የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን በተዘዋዋሪ ለመገልገል የሚውሉትን የቪፒኤን መተግበሪያዎችን ፍላጎት እና ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይነገራል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *