በአዲስ አበባ በዓድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ህግ በጣሱ ፖሊሶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

በአዲስ አበባ በዓድዋ ድል በዓል አከባበር ላይ ህግ በጣሱ የፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ።

በዘንድሮው የአድዋ በኣል በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ የጸጥታ ሀይሎች በዜጎች ላይ ያልተገባ ድርጊት መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ እና ሌሎችም ተቋማት መናገራቸው ይታቀሳል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጉዳዪ ዙሪያ ዛሬ በሰጠው መግለጫ በዕለቱ የህግ ጥሰት በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ኮሚሽኑ አክሎም በዓሉ በተከበረበት እለት የከተማዋን ሰላም አውከዋል በሚል 878 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር አውያለሁ ብሏል።

በህግ ቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥም 557ቱ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንዳሉት የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር ያልተገባ ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን እና ሌሎች የምርምራ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

127ኛው የዓድዋ ድል በዓል ደማቅ በሆነ መንገድ በሰላም ተጠናቆ መንገዶች ለተሽከርካሪ ክፍት መሆን ሲጀምሩ በተለይ በምኒልክ አደባባይ ችግሮች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የበዓሉን አውድ ለመቀየርና የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ ለማደፍረስ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት ለመፍጠር መሞከራቸውን ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

በዕለቱ በተተኮሰ ጥይት የአንድ ግለሰብ ሕይወት ማለፉን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ምርመራና የማጣራት ስራ እየተከናወነ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

በፈረስ ላይ የነበረ ግለሰብ ላይ ያልተገባ ድርጊት በፈጸመው የፖሊስ አባል ላይም ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።

ይሁንና ህግ ጥሰዋል በተባሉ የፖሊስ አባላት ላይ ምን አይነት እርምጃ እንደተወሰደ ኮሚሽነሩ አልጠቀሱም።

በዕለቱ 16 የፖሊስ አባላት ቀላልና ከባድ ጉዳት ሲደርስባቸው ሦስት አውቶቡሶችና አንድ አምቡላንስም መሰባበራቸውን ኮሚሽነሩ አንስተዋል ተብሏል።

የአድዋ በዓልን ለማክበር በአዲስ አበባ ምኒልክ አደባባይ ለመጓዝ የፈለጉ ነዋሪዎች ማለፍ እንዳይችሉ በጸጥታ ሀይሎች መከልከላቸውን የአይን እማኞች በዕለቱ ለአልዓይን መናገራቸው ይታወሳል።

የመንግስት ኮሙንኬሽን ሚንስትር ዴዔታ አቶ ከበደ ደሲሳ በበኩላቸው በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን ጠቅሰው ወደ ተባለው አደባባይ እንዳያልፍ የተከለከለ ሰው የለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተውም ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ግን የጸጥታ ሀይሎች ያልተመጣጠነ ሀይል መጠቀማቸውን እና በንጹሀን ዜጎች ላይ የህግ ጥሰት ፈጽመዋል ሲሉ ድርጊቱን መኮነናቸው አይዘነጋም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *