የኢትዮጵያ ሞርጌጅ ባንክ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ተገለጸ

ዜጎች በባንክ በኩል ቤት ገዝተው በየወሩ የሚከፍሉበትን የሞርጌጅ ሥርዓት ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በሰጡት ማብራሪያና ምላሽ፣ በቤት ግንባታው ሂደት የቱርክ፣ የቻይናና የኮሪያ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ቤቶችን የሚገነቡ የፋብሪካ ሂደቶች እየተሞከሩ ነው።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ከ10 እስከ 15 ወለል የሚደርሱ ሕንፃዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመገንባት እየተሰራ ሲሆን፣ በ15 ቀናት ወይም በአንድ ወር ውስጥ ቪላ ቤቶችን ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎችን ወደ ሀገር ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው።

ይሁን እንጂ ፋብሪካዎችን መምረጥና መግዛት፣ የግንባታ ግብዓቶችን ማዘጋጀትና ወደ ግንባታ ቦታዎች ማድረስ እንዲሁም ከግንባታው ጋር የተያያዙ የፍሳሽ መስመርና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን በተሟላ ሁኔታ ማስተካከል አንዳንድ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

በአንዳንድ የሙከራ ግንባታ ቦታዎች የተከሰቱ ችግሮችን መልሶ በመገምገም ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

በገጠርና በከተማ የቤት ግንባታ ሥራዎች በስፋት መጀመራቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቤት ግንባታው ዕቅድ እንደሚሳካ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በተለይ የዜጎች የገቢ አቅም ውስን መሆን ቤት በቀጥታ ገዝቶ መኖር ለብዙዎች አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በባንክ በኩል ቤት በመግዛት በየወሩ እየከፈሉ የሚኖሩበትን የሞርጌጅ ሥርዓት መዘርጋት ተጨማሪ የሥራ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።

የሞርጌጅ ሥርዓቱን ለማስፈጸም ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንና በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ ባንኩ መቼ ስራ እንደሚጀምር ግን አልተናገሩም።

በአጠቃላይ የመንገድ፣ የባቡርና የቤት ግንባታን ጨምሮ መሠረተ ልማቶችን በቅድሚያ በማከናወን ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እያደገ ያለው ኢኮኖሚ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በተግባር የሚያስፈጽማቸው ሥራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *