በአዲስ አበባ ከተማ ከ1997 እስከ 2007 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት በበቁ የጋራ መኖሪያ (ኮንዶሚኒየም) ሕንፃዎች ላይ የተስተዋሉ የግንባታ ጥራት ጉድለቶችን በሙያዊ አሰራር ለማስተካከል የሚያስችል ሥራ ሊጀመር መሆኑን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል።
ኮርፖሬሽኑ እንደገለጸው በአስርቱ ዓመታት ውስጥ በተገነቡት ሕንፃዎች ላይ የተከሰቱትን ችግሮች ዓይነትና የጉዳት ደረጃ በጥናት ለመለየት ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ሰፊ ሳይንሳዊ ምርምር ተካሂዷል።
በተካሄደው ጥናት መሠረት ቅድሚያ የጥገናና የማስተካከያ እርምጃ የሚያስፈልጋቸው ሕንፃዎች የተለዩ ሲሆን በነዋሪዎች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ ሳይደርስ እርምቱ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ኮርፖሬሽኑ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት በማድረግና አስፈላጊዎቹን የሥራ ተቋራጮች በመመደብ ሥራውን ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ጥራት የጎደለው ግንባታ ባካሄዱ አካላት ላይ የተጠያቂነት አሰራር እንደሚዘረጋ ተጠቅሷል። በጥናቱ የተገኙ ጉድለቶችን መሠረት በማድረግ አስፈላጊው የሰነድና የማስረጃ ዝግጅት መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን በውል ግዴታቸው መሠረት ባልሰሩ አካላት ላይ ተገቢው የሕግና የውል እርምጃ እንደሚወሰድ ኮርፖሬሽኑ አረጋግጧል።
በሌላ በኩል፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለመመለስ ባከናወነው የለዉጥ ሥራ 496 ሺህ 971 ቤቶችን ገንብቶ ማስተላፉን አሳውቋል።
በ2018 በጀት ዓመትም በተለያዩ ሳይቶች በግንባታ ላይ የሚገኙ ቤቶች የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎላቸው ፣ የሥራ ፍጥነታቸውና የግንባታ ጥራታቸው ተጠብቆ ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ መሆኑ ተጠቅሷል።