የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሐምሌ 6 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው 7ኛ ስብሰባው፣ የተለያዩ የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቦ ማጽደቁን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ያለመ አዳዲስና ወሳኝ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ማሳለፉን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።
ኮሚቴው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በሀገር ውስጥ ምርቶች ላይ የሚያሳድረውን ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መወሰኑንም ገልጿል።
እስካሁን ባንኮች በሚሰጡት ብድር ላይ ተጥሎ የነበረው የ24 በመቶ ቀጥተኛ የብድር ዕድገት ገደብ ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ተወስኗል።
በባንኮች ላይ የብድር ገደብ ውሳኔ ተጥሎ የነበረው ኢኮኖሚው በወለድ ምጣኔ ላይ ወደተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት እስኪሸጋገር እንደነበር በማስታወስ ውሳኔው ግቡን መምታቱን ጠቅሷል።
የብድር ገደብ መነሳቱን ጥብቅ የሆነ የፖሊሲ እርምጃ በማስፈለጉ ፣ ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ወለድ ምጣኔውን በ1.0 በመቶ በማሳደግ ከነበረበት 15 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል መወሰኑንም ገልጿል።
የወጪ ንግድን ተወዳዳሪነት ለመጨመርና በገበያው ላይ እምነት ለመገንባት፣ ላኪዎች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ለባንኮች እንዲሸጡ የሚደረገው የውጭ ምንዛሬ ድርሻ ከነበረበት 50 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።ይህም ላኪዎች ካገኙት የውጭ ምንዛሬ 70 በመቶውን እንዲጠቀሙ ዕድል ይሰጣል።
ከአስመጪዎች ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ለመቀነስና የዋጋ ንረትን ለመግታት፣ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ የሚወስደው የ2.5 በመቶ ኮሚሽን ወደ 1.5 በመቶ እንዲቀንስ መወሰኑንም ብሔራዊ ባንክ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የብድር መስፋፋት በዋጋ ንረት ላይ አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር፣ ብሔራዊ ባንክ የባንኮችን የብድርና ቁጠባ ጥምርታ መሠረት ያደረገ የተለየ የመጠባበቂያ ተቀማጭ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚያደርግም ባንኩ አስታውቋል።