የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የከፍተኛ ትምህርት ማስረጃ አሰጣጥንና የደረጃ ግምገማ ሂደትን ለማሻሻል ያስችላል የተባለውን አዲስ ረቂቅ መመሪያ ለህዝብ አስተያየት ክፍት አድርጓል።
ባለስልጣኑ “የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ እና የአቻ ግመታ መመሪያ ቁጥር 990/2016” ላይ ማሻሻያ ለማድረግ በተዘጋጀው በዚህ ረቂቅ ላይ የትምህርት ማህበረሰቡና ባለድርሻ አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት ጥሪ አቅርቧል።
ተቋሙ እንዳስታወቀው ይህ መመሪያ ያስፈለገው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት ማስረጃዎችን የማረጋገጥ ሂደት ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ እና ግልጽ ለማድረግ በሚል ነው።
በተለይም በደረጃ ግምገማ እና በማስረጃ ማረጋገጫ ሂደት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ታልሞ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
ይህ መመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የመንግስትም ሆነ የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተምረው ከ2010 ዓ.ም እስከ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለተመረቁ ተማሪዎች ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
ለዲግሪ ትምህርት ከመግባታቸው በፊት የሙያ ብቃት ማረጋገጫ (COC) ፈተና ሳይወስዱ ዲግሪ የተማሩ እና የተመረቁ እንዲሁም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የወሰዱት ለዲግሪ ትምህርት ከተመዘገቡ በኋላ የሆኑ ተማሪዎችንም ያጠቃልላል።
በተጨማሪም የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ማስረጃ ለማረጋገጥ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወይም በፌደራል ወይም በክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም የተረጋገጠ ኦሪጅናል የስልጠና ማስረጃ ወይም ዲፕሎማ እና ትራንስክሪፕት ላላቸው ነገር ግን የደረጃ አራት የብቃት ማዕቀፍ ለሌላቸው በመጀመሪያ ዲግሪ ተምረው የተመረቁ ተመራቂዎች የትምህርት ማስረጃቸው እንዲረጋገጥላቸው በዚሁ ረቂቅ መመሪያ ላይ ተጠቅሷል።
የመጀመሪያ፣ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ዲግሪ (ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2015 ዓ.ም) የያዙ ተማሪዎች ሚኒስትሩ በሚያዘጋጀው በያዙት የትምህርት ደረጃ የሚሰጥ ፈተና ላይ ተቀምጠው ማለፍ ይኖርባቸዋልም ተብሏል።
ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የተመረቁ ተማሪዎች የትምህርት ማስረጃቸው የሚረጋገጠው የመውጫ ፈተና (Exit Exam) ወስደው ያለፉ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ይህ መመሪያ ተሻሽሎ በስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ያለበት ትምህርት ሚኒስቴር ወይም ማንኛውም የሚመለከተው አካል የሚያወጣውን የመግቢያ መስፈርት ብቻ ተከትሎ ይሆናል ተብሏል።
በመመሪያው ትርጋሜ መሰረት በያዙት የተምህርት ደረጃ ፈተና መስጠት“ ማለት የደረጃ አራት የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖረው የመጀመረያ ዲግሪ ፣ ሁለተኛ ዲግሪ ወይም ሶስተኛ ዲግሪ ይዘው የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ አሁን የደረሱበት ወይም የያዙት ዲግሪን መሰረት ተደርጎ የሚሰጥ ፈተና ሆኖ ፈተናውን ሲያልፋ የትምህርት ማስረጃቸውን ለማረጋገጥ ይሆናል።
ባለስልጣኑ ይህ ረቂቅ መመሪያ ከመጽደቁ በፊት በይፋ ለውይይት ያቀረበው ሲሆን በረቂቁ ላይ የአስተያየት መስጫ ጊዜ ከሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚሆን ተገልጿል።