መንግስት በቀጣዩ ዓመት 1 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገለጸ

የፌደራል መንግሥት በአዲሱ 2019 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ 817 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታዉቋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የ2019 በጀት ዓመት የበጀት መግለጫ ማብራሪያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ በ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት በጥቅሉ አንድ ነጥብ 8 ትሪሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡

ይህ የገቢ ዕቅድ በ2018 በጀት ዓመት ይሰበሰባል ተብሎ ከተገመተው ጠቅላላ ገቢ አንጻር የ17 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ያለው ሆኗል።

እቅዱ ከዓመታዊ በጀት  ውስጥ የ89  በመቶውን ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ለመሰብሰብ መታቀዱንም ሚንስትሩ አቶ አህመድ ጠቁመዋል።

የታክስ ገቢ ዕቅዱን ለማሳካትም በታክስ ፖሊሲና በታክስ አስተዳደር ረገድ የተያዙ ማሻሻያዎችን፣ የታክስ ዲጂታላይዜሽንና የኤክሳይዝ ስታምፕ አሠራርን በተጠናከረ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ በጀት ጉድለት መሸፈኛ የሚወሰደው ብድር ሙሉ በሙሉ ቆሟል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህም የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ማገዙን ተናግረዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት በምግብ ዘይትና በመሠረታዊ ሸቀጦች እንዲሁም መድኃኒቶችን በተመሳሳይ የድጎማ በጀት በመመደብ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ የ2019 በጀት ዓመት የ10 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚመዘገብ ግምት የተቀመጠ ሲሆን ፤ በኢኮኖሚ እድገቱ ኢንዱስትሪ አገልግሎት ዘርፍና ግብርና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡

የፌደራል መንግስት ለ2019 በጀት የ2  ነጥብ 3 ትሪሊዮን ብር ጠቅላላ በጀት መያዙ ሲገለጽ ከዚህ ውስጥ 542 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን፤ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ዕዳ ክፍያ እንደሚውል ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *