የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ጥሎት የነበረውን የቪዛ ገደብ ከሁለት ዓመት በኋላ አንስቻለሁ ብሏል፡፡ ህብረቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ ሚያዝያ 2016 ወደ አውሮፓ በሚጓዙ ኢትዮጵያውያን ቪዛ አመልካቾች ላይ ገደቦችን ጥሎ እንደነበር ገልጾ ገደቡ መነሳቱን አስታውቋል፡፡
ህብረቱ የቪዛ ገደቦቹን የጣለው በተለያዩ ጊዜያት ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት የገቡ እና የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያዊያንን የኢትዮጵያ መንግስት ለመመለስ እየተባበረ አይደለም በሚል ምክንያት ነበር፡፡
ከሁለት ወራት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮጵያ እና አውሮፓ ህብረት የሁለትዮሽ ውይይት ላይ በአውሮፓ ሀገራት የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ከመመለስ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት ያሳየውን መሻሻል አድንቆ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ከጣላቸው የቪዛ ገደቦች መካከልም የቪዛ ማመልከቻ ጊዜ ከ15 ቀን ወደ 45 ቀናት ከፍ ማድረግ፣ ቪዛ ያገኙ ኢትዮጵያዊን ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳይጓዙ ወይም የድግግሞሽ ጉዞዎችን አለመፍቀድ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ዲፕሎማቶች ያለ ቪዛ ወደ አውሮፓ እንዲገቡ የሚፈቅደውን አሰራርም በማስቀረት በክፍያ እንዲስተናገዱ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ህብረቱ ባስተላለፈው አዲስ ውሳኔ ዙሪያ እስካሁን ያለው ነገር ባይኖርም አውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የጣለው የቪዛ ገደብ እንዳሳዘነው ገልጾ እና ወደ አውሮፓ ከተሞች በተለያዩ ምክንያቶች ተጉዘው የመኖሪያ ፈቃድ ያላገኙ ዜጎቹን ለመመለስ ተባባሪ አይደለም በሚል የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጎ ነበር፡፡
ህብረቱ በኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የቪዛ ገደብ ውሳኔ መልሶ እንዲያጤነው የጠየቀው ሚኒስቴሩ የንገድ እና ልማት ዋነኛ አጋሩ ከሆነው የአውሮፓ ህብረት ጋር በጋራ መስራቱን እንደሚቀጥል መግለጹ አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም የቪዛ አገልግሎቱ ወደነበረበት እንዲመለስ የጋራ ውይይቶችን ማድረጉን እንደሚቀጥልም በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ጠቅሶ ነበር፡፡