በአሁኑ ሰዓት በማርበርግ ቫይረስ መያዙ የተረጋገጠ በሕይወት ያለ ሰዉ አለመኖሩን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስካሁን ድረስ የሶስት ሰዎች ህይወት በማርበርግ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸዉን ማጣታቸውንም ሚኒስቴሩ ጠቅሷል።
ጤና ሚኒስቴር የማርበርግ በሽታ አስመልክቶ በዛሬው ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ከተማ የማርበርግ በሽታ መከሰቱን ካሳወቀበት ህዳር 3 ጀምሮ የበሽታዉ ምልክት ያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸዉ የተባሉ ሰዎችን ቦታዎች ላይ የመለየት ስራ እየሰራ ይገኛል።
ሚኒስቴሩ እስካሁን ድረስ 17 የላብራቶሪ ናሙና ወስዶ የመረመረ ሲሆን፤ በሶስት ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ስድስት ሰዎች የበሽታዉን ምልክት አሳይተዉ ህይወታቸዉ ቢያልፍም በላብራቶሪ የተረጋገጠዉ ግን ሶስት ሰዎች ላይ መሆኑን እና እነሱም ህይወታቸዉ ማጣታቸዉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ በሕይወት ያለ ሰዉ እንደሌለም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
በሽታዉን ለመከላከልም የድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና ተቋማት መቋቋማቸዉን እና የላብራቶሪ ግብአቶችና ባለሙያዎች ወደ ቦታዉ መላካቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ቁሳቁሶችና መድኃኒቶችን የማሟላት ዝግጅት መጠናቀቁና ግብአት የማሟላትና የማሰራጨት ስራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በበሽታዉ ህይወታቸዉን የሚያጡ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን የቀብር ስነ ስርዓት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚሰጠዉ መመሪያ መሰረት መፈጸም እንደሚኖርበትም ጠቁመዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተው እና ምንነቱ ለማረጋገጥ የዘረመል ምርመራ ሲካሄድበት የቆየው ሄሞራጂክ ፊቨር በሽታ መንስኤ ማርበርግ ቫይረስ (Marburg Virus) ስለመሆኑ መረጋገጡን፤ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ ማሳወቃቸው ይታወቃል።
ሕብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግና ከሌሎች ሕመሞች የሚለይበትን መንገድ ማወቅ ይገባል ያሉም ሲሆን፤ ምልክቱ ከታየባቸው ሰዎች ጋር የሚደረግ ንክኪ መተላለፊያ መንገዱ ነው ብለዋል።
ማርበርግ ቫይረስ በትንፋሽ የሚተላለፍ አለመሆኑና ለመከላከል ንክኪን መቀነስ እጅን መታጠብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ሰዓት በዚህ በሽታ የተያዙ ታማሚዎች አለመኖራቸውን የገለጹት ዶ/ር መቅደስ፤ ይህ ማለት የሚያዘናጋ አለመሆኑንና የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እና ባለበት እንዲቆም ለማድረግ በርካታ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የማርበርግ ቫይረስን ለመቆጣጠር የመጀመሪያው መንገድ መከላከል ሲሆን፤ ምልክቶች የታዩባቸውን ሰዎች ሕክምና ለመስጠት ፈሳሽን የመተካት እና እንደ ሕመሙ ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
ነገር ግን ለዚህ ይሆናል ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠለት መድሃኒት አለመኖሩን ተናግረዋል።
በተለያዩ ሀገራት በሙከራ ደረጃ ላይ ያሉ መድሃኒቶችና ክትባቶች መኖራቸውና ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ማለፍ ያለባቸው ሂደቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የማርበርግ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርመን ሀገር በአውሮፓውያኑ 1967 መታየቱን አስታውሰዋል።
ከዛ በኋላ በ12 ሀገራት ላይ የታየ ሲሆን፤ በአፍሪካ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ጋና፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ላይ መታየቱን ጠቁመዋል።
ቫይረሱ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሲከሰት ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም ሚኒስትሯ ጨምረው ገልጸዋል።
ሕብረሰተቡ መረጃዎችን እና የጥንቃቄ መንገዶችን ከጤና ሚኒስቴር እንዲሁም ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መከታተል እንዳለበትም አሳስበዋል።
የማርበርግ ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተበት ጅንካ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ቫይረሱ መከሰቱን ለሚዲያ አጋልጠዋል የጠባሉት ሰው ከሀላፊነት መነሳታቸው ተገልጿል፡፡ ስራ አስኪጁ ከሀላፊነት የተነሱት ለሚዲያ ማሳወቁ ስህተት ነው በሚል እንደሆነም ተገልጿል፡፡