በክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች ጭምር በመታገዝ ህገ ወጥ የምንዛሬ ዝውውር ያደርጉ ነበር የተባሉ ቻይናውያን በቁጥጥር ስር ዋሉ
በተቀናጀ መንገድ ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ አሻጥሮችን ሲፈጽሙ ደረስኩባቸው ያላቸውን 112 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ያስታወቀው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት 8 ቻይናውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ለመንግሥት ብዙሀን መገናኛዎች በላከው መግለጫ ይፋ አድርጓል።
በመግለጫው በተደራጀ መንገድ በስውር ሲፈጸም ነበር ያለውን ህገ ወጥ የምንዛሬ ገንዘብ ዝውውርና አሻጥር ለማምከን የሚያስችል ምስጢራዊ የመረጃ ስምሪቶችን ሲያደርግ እንደቆየ ያስታወቀው አገልግሎቱ ቻይናውያኑን ጨምሮ 112 ኢትዮጵያውያንና የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፤ ከሕገ – ወጥ ተግባሩ ጋር ትስስር የነበራቸው አምስት መቶ አስራ ዘጠኝ የባንክ አካውንቶች መታገዳቸውን እንዲሁም የተለያዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
ሕገ- ወጥ ሃዋላዎች ፣ የገንዘብ ዝውውሮች፣ የውጭ ምንዛሪ ስወራዎች ፣ የግብር ስወራዎች፣ ሕገ- ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ የማስመሰልና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ እንዲሁም አሸባሪዎችንና የታጠቁ ቡድኖችን ለመደገፍ ሲውሉ መቆየታቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡
በተለይም ሕገ- ወጥ በሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፤ ሕገ- ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎች፤ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያዎች፤ ሕገ-ወጥ የሃዋላ አዘዋዋሪዎችና ደላላዎች፤ በወጪና ገቢ ንግድ ላይ አሻጥር የፈፀሙ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ሕጋዊ ንግድ ሳይኖራቸው በሕገ-ወጥ ሃዋላ ላይ በመሰማራት ከፍተኛ ገንዘብ በማንቀሳቀስ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሱ አካላት የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሚልኩት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ የብሔራዊ ባንክን መመሪያ በሚጥስ ሁኔታ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያስከትሉ የቆዩ ሕጋዊ ፈቃዳቸው በፈጸሙት ተደጋጋሚ ጥፋት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰረዘባቸው ዓለም አቀፍ የሃዋላ አስተላላፊዎችና ሕገ-ወጥ የሃዋላ ድርጅቶችም እርምጃው የተወሰደባቸው ናቸው።
በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ሕገ- ወጥ የውጭ ምንዛሪ ማስተላለፊያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም ሀብትን ከሀገር በማሸሽ ላይ ያሉ ድርጅቶች ባለቤቶችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የብሔራዊ ባንክ ሕግን በሚጥስ ሁኔታና ያለምንም ፈቃድ የክሪፕቶ ከረንሲ መተግበሪያን በመጠቀም በሕገ- ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪን ሲያዘዋውሩ የነበሩ አካለት ላይም እርምጃ መወሰዱንም መግለጫው ያመለክታል፡፡
በሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም ላይ በማነጣጠር ሲፈጸም የነበረው ኢኮኖሚያዊ አሻጥር ትላልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማስተጓጎል፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ እንዲያድርበት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ በተቀናጀ መንገድ ሲፈጽሙት የነበረ መሆኑንም አንስቷል፡፡
የሀገርን ደኅንነት ስጋት ላይ በሚጥሉ እና የሀገርን ኢኮኖሚ በሚጎዱ አሻጥሮች ላይ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን በመከታተል የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢቢሲ የተላከው መግለጫ፤ መላው ሀገር ወዳድ ዜጋ መሰል ወንጀሎችንና ወንጀለኞችን በማጋለጥ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ በተለያዩ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ጋር ተወያይተው ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ በተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ሳውዲ አረቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ከተሞች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ጋር ተወያይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከሬሚታንስ ገቢ እየተገኘች ያለው ገቢ 7.2 ቢሊየን ዶላር ብቻ ነዉ ብለዋል።
አቶ አቤ ሳኖ እንዳስረዱት፣ አሁን ካለው የገንዘብ ፍሰት ቀሪው 78 በመቶ የሚሆነው ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ እንዳልሆነም ተናግረዋል።
የዳያስፖራውን ሙሉ አቅም በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ግን፣ ኢትዮጵያ በዓመት ከ35 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከሬሚታንስ ገቢ ልታገኝ እንደምትችል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተባበሩት አረብ ኢምሬት ከተሞች አቡ ዳቢ እና ዱባይ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ገንዘባቸውን በቀላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲልኩ ቦቲም ከተሰኘው የገንዘብ ማስተላለፊያ መተግበሪያ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡
እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች መረጃ ከሆነ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሲሆን አብዛኞቹ በመካከለኛው ምስራቅ፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ይኖራሉ።
ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይኖርባቸዋል።
የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዚህ በፊት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከሬሚታንስ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ብቻ ገቢ ማግኘቷን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ከተሞች ሆነው ህገወጥ የሬሚታንስ ገንዘብ ዝውውርን ይፈጽማሉ ያለቻቸውን ድርጅቶች ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ በህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው ካልታቀቡ አካውንት ከመዝጋት ጀምሮ ገንዘባቸው እንደሚወረስም ተገልጿል።
#finance