ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በህወሀት ምክንያት መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናገሩ

የሀገር መከላከያ ሰራዊት አዛዥ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለማሰብ በሚል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ህወሀትን ተችተዋል።

ፊልድ ማርሻል በዚህ ጊዜ እንዳሉት መከላከያ ሠራዊት ሕይወቱን ከሰጠለት ሕዝብ ውስጥ የወጡ ጥቂት ካሃዲዎች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከኋላው መውጋታቸው ሕመሙ ጥልቅ ነው ብለዋል።

በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመው ክህደት ወንድም ወንዱሙ ላይ የፈፀመው ክህደት በመሆኑ በታሪክ ልዩ እንደሚያደርገውም ጠቅሰዋል።

የትግራይ ሕዝብ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ክህደት አይቀበለውም ያሉት አዛዡ  የትግራይ ሕዝብ በልጆቹ ክህደት አፍሮ፣ ተመልሰን መቐለ ስንገባ አጨብጭቦ ተቀብሎን ነበር ሲሉም አክለዋል።

ስለዚህ ክህደት እና አስነዋሪ ታሪክ ስናውራ ስለ ጥቂት የሕወሓት አመራሮች እንጂ ስለ ትግራይ ሕዝብ እንዳልሆነም ገልጸዋል።

የህወሀት ጀነራሎችን “ጉጅለ” እያሉ የጠሩት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ በሻዕቢያ ተቀጥሮ ሀገር ያስገነጠለ እና የባህር በር ያሳጣን ነው ሲሉም የሰላ ትችት ሰንዝረዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ አክለውም “የእኛ ጥያቄ አድጓል፤ ይታፈን የነበረው የባህር በር ጥያቄ ወደ ፊት መጥቷል፣ መከላከያ ሠራዊት የሚዋጋው ለሥልጣን አይደለም፤ እኛ እዚህ ያለነው አባቶቻችን የሰጡንን ሀገር ለልጆቻችን ለማስተላለፍ ነው” ብለዋል።

“አንቸኩልም፤ ጦርነት አንፈልግም፤ አንቀሰቅስም። በልማታችን ላይ የመጣውን ግን መመከት አለብን፤ የታጠቅነውም ለዚህ ነው” ሲሉም በዝክረ ሰሜን እዝ ፕሮግራም ላይ ተናግረዋል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ስር ባለው እና በመቀሌ በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ በህወሀት ታጣቂዎች ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተቀሰቀሰው።

ለሁለት ዓመት በዘለቀው በዚህ ጦርነት ከ800 ሺህ በላይ ዜጎች ህይወት እንዳለፈ ሲገመት 20 ቢሊዮን ዶላር ንብረት ወድሟል ተብሏል።

በፌደራል መንግስት እና የትግራይ ሀይሎች መካከል በተካሄደው በዚህ ጦርነት በተለይም ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ክፉኛ ተጎድተዋል።

ጦርነቱ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የቆመ ቢሆንም ስምምነቱ በሚገባ ባለመፈጸሙ ሁለቱ አካላት ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ተሰግቷል።

የአውሮፓ ህብረት ከሰሞኑ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዲፈጸም አሳስቧል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *