የቪዛ ጊዜያቸውን ያሳለፉ ከ36 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ተቀጡ

በኢትዮጵያ የተሰጣቸውን የቪዛ ጊዜ ያሳለፉ ከ36 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ተቀጥተው ወደ ሕጋዊ መስመር ተመልሰዋል አለ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፡፡

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እንዳሉት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ሕግ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ እየተሰራ ነው፡፡

በዘርፉ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ሀገራዊ አቅም መጠናከሩን አመልክተዋል፡፡

ለአብነትም በአዲስ አበባ በተካሄዱ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ጉባዔዎች የተሳተፉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ያለምንም እንከን መስተናገዳቸውን ጠቅሰዋል።

በቪዛ አገልግሎት ወደ 188 ሀገራት የመዳረሻ (ኦን አራይቫል ቪዛ) ተጠቃሚዎች ሆነዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ÷ ይህም የ24 ሰዓት የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ አገልግሎት ያለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ከፓስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተለያዩ የማሻሻያ ርምጃዎች መወሰዳቸውን እና በዚህም በሕገ ወጥ ሰንሰለት የተሰማሩ 26 ሰዎች ተጠያቂ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተሰጣቸውን የቪዛ ጊዜ ያሳለፉ ከ36 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች ተቀጥተው ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲመለሱ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 4 ሚሊየን ፓስፖርት ለመስጠት በቂ ዝግጅት መደረጉንም ወ/ሮ ሰላማዊት አጽንአት ሰጥተዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ህገወጥ እና ሀሰተኛ ሰነዶችን የያዙ የውጭ ሀገር ዜጎችን ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

ተቋሙ በወቅቱ ሀሰተኛ ሰነዶችን ተጠቅመው ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ደርሼበታለሁ ብሎም ነበር፡፡

የውጭ ሀገር ዜጎች ሀሰተኛ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ሀሰተኛ ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ሀሰተኛ ፓስፖርት፣ ሀሰተኛ ቪዛ እና ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየኖሩ መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ይህን ተከትሎም በተደረገው የማጣራት ስራ ከ18 ሺህ በላይ ሀሰተኛ ጊዚያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሀሰተኛ ቪዛ እና ከአንድ ሺህ 800 በላይ የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያን ያሰሩ ዜጎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መገኘታቸው ተቋሙ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለጉብኝት እና ሌሎች ጉዳዮች ወደ ግዛቷ በሚገቡ ዜጎቿ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የጀመረች ሲሆን የቪዛ ቆይታቸው ያለቀባቸው ዜጎች በቀን ከ30 ዶላር በላይ ቅጣት ጥላለች፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *