ለህዳሴው ግድብ ግንባታ 233 ቢልዮን ብር ወጪ መደረጉ ተገለጸ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 233 ቢልዮን ብር ወጪ መደረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምርቃትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የተቋሙ የኮርፖሬት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ በአጠቃለይ 233 ቢልዮን ብር ወጪ ተደርጓል።

ከዚህ ውስጥ 223 ቢልዮን ወይም 91 በመቶ የሚሆነው ወጪ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘ ነው ብለዋል።

ከመላው ኢትዮጵያዊያን በቦንድ ግዢ 18 ነጥብ 9 ቢልዮን ብር የተሰበሰበ ሲሆን፤ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን 1 ነጥብ 6 ቢልዮን ብር መሰብሰቡንም አቶ ሞገስ አብራርተዋል።

እንዲሁም 3 ነጥብ 2 ቢልዮን ብር በስጦታ የተገኘ መሆኑን አንስተዋል።

ላለፉት 14 ዓመት በግንባታ ላይ የቆየው የህዳሴው ግድብ የፊታችን ማክሰኞ ጷግሜ  4 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ እንደሚመረቅ ይጠበቃል።

የውሀ እና ኢነርጂ ሚንስትር ሀብታሙ ኢተፋ ከሪፖርተር መጽሄት ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ላይ እንዳሉት በታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅት 15 ሺህ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

ህይወታቸውን ካጡ ዜጎች መካከል የቀድሞው የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ አንዱ ሲሆኑ ለብቻቸው መታሰቢያ ሀውልት እንደማይቆምላቸውም ሚንስትሩ ተናግረዋል።

“የጸጥታ ሀይሎች፣ ሹፌሮች፣ ሰራተኞች እና ሌሎሽም የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወታቸውን አጥተዋል ስለዚህ ይህ በሆነበት ሁኔታ ለግለሰቦች የተለየ መታሰቢያ ሀውልት የለም” ሲሉም ሚንስትሩ በቃለ መጠይቁ ወቅት ገልጸዋል።

በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቁጥር አንድ የሆነው የህዳሴው ግድብ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚመረቅ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በኢትቪ በተላለፈ ንግግራቸው ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ እና ሀይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ምስጋና ከቀረበላቸው የቀድሞ መሪዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *