የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ሰነዶች ሽያጭን በይፋ አስጀምረዋል።
የገንዘብ ሚንስቴር ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ጊዜ እንዳሉት መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ የግምጃ ቤት ሰነዶችን ለገበያ ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት ውስጥ መንግስት ከበጀተው 1.9 ትርሊዮን ብር ውስጥ 188 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት እንዳለበት ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
ከገጠመው የበጀት ጉድለት ውስጥም 173 ቢሊዮን ብሩን ግምጃ ቤት ሰነድ ለሽያጭ በማቅረብ ለመሰብሰብ መታቀዱንም አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ብድሩ ከሰነድ ገዢዎች የሚሰበሰበው የዋጋ ግሽበትን በማያባብስና የማክሮ ኢኮኖሚውን በማያናጋ መልኩ እንደሚሆንም ገልጸው ነባር የግምጃ ሰነዶችን ወደ ኤሌክትሮኒክስ መንገድ ስራዎች እየተቀየሩ መሆኑን፣ አዳዲስ ግምጃ ሰነዶችም በዚህ መልኩ ለገበያ ይቀርባሉም ብለዋል አቶ አህመድ ሽዴ ፡፡
የኢትዮዽያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው በዛሬው ዕለት ለ182 ቀናት የሚቆይ የመንግስት ግምጃ ቤት ሰነዶች፣ ወጋገን እና ገዳ ባንኮች አክስዮኖችን ማገበያየት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት ኢትዮጵያዊያን ግለሰቦችና ተቋማት በኢንቨስትመንት ባንኮች አማካኝነት ሰነዶችንና አክስዮኖችን መግዛትና መሸጥ እንደሚችሉ ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
አሁን ላይ ከ4700 ብር ጀምሮ የመንግስት እዳ ሰነድ እንዲሁም የባንክ አክስዮኖችን ደግሞ ከአንድ ሺህ ብር ጀምሮ መግዛት ይችላሉ ያሉት ጥላሁን ለዚህ የሚረዳ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት መገንባቱንም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ከንግድ እና ልማት ባንኮች እንዲሁም ከመንግስታዊው አንድ የኢንሹራንስ ተቋም በስተቀር ሁሉም ባንኮች አክስዮኖቻቸውን ለሽያጭ ይመጣሉ ብለው እየጠበቁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ገበያ 50 ኩባያዎችን በ10 ዓመታት ውስጥ ደግሞ 90 ኩባንያዎችን ሊስት የማድረግ እቅድ እንዳለው የገለጸው ተቋሙ በቀጣይ የመንግስት የልማት ድርጅቶችም ወደ ገበያ ሊመጡ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው የካፒታል ገበያ በዚህ መልኩ መደራጀቱ የገንዘብ ፖሊሲ ውጤትማነትን ለማሳካት ፤ የዋጋ ግሽበትን ለማውረድ እና ብሔራዊ ባንኩ ለሚወስዳቸው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ እርምጃዎች እንደሚጠቅሙ ገልጸዋል።
የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ ወደፊት እንዲመጣና የበለጠ እየጠነከረ እንዲመጣ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ገዢው የበጀት ጉድለትን ለመሙላት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡