ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከቀጣዩ መስከረም ወር ጀምሮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነዳጅ ለገበያ እንደምታቀርብ መናገራቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ካሉ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ከመስከረም ወር ጀምሮ ነዳጇን ለገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰባት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ ነዳጅ ማውጣት ጀመረች በሚል ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
ይሁንና ይህ ከሆነ ከሰባት ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ነዳጅ ለገበያ እንደምታቀርብ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሶማሊ ክልል ኦጋዴን አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ እንዳላት በተደጋጋሚ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን የቻይና ፖሊሲጂኤል ኩባንያ ነዳጅ ለማውጣት በሂደት ላይ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎቷን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ሀገራት በማስገባት በመሸፈን ላይ ስትሆን በዓመት ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከሁለት ወራት በኋላ እንደሚመረቅም በዚሁ ከሚዲያ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሶስት ወራት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ባደረጉት ውይይት የህዳሴው ግድብን ከ6 ወር በኋላ እንመርቃለን ብለው ነበር፡፡
ከ15 ዓመት በፊት ለግንባታው መሰረት ድንጋይ ሲጣል 80 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል ተብሎ የተጀመረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ ግንባታው 97.6 በመቶ እንደደረሰና ጥቂት የማጠናቀቂያ ስራዎች ብቻ እንደቀሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተናግሯል፡፡
ህዝቡ እስካሁን ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ በበጎ ፈቃደኝነት ያዋጣ ሲሆን በዚህ ዓመት 1.6 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሀይል መጠን ከአፍሪካ ግዙፉ ፕሮጀክት የሆነው የህዳሴው ግድብ በአሁኑ ወቅት በሁለት ተርባይኖች 540 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ ግድቡ የያዘው የውሃ መጠን 42 ቢሊዮን ሜትር ኪዉብ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅ የሚይዘው ውሃ መጠን ወደ 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከፍ ይላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የህዳሴው ግድብ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 80 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።
በሀይል ማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ግድብ የሆነው የሕዳሴው ግድብ በአጠቃላይ ሀይል የሚያመነጩ ሰባት ዩኒቶች ይኖሩታል ተብሏል።
ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ በአባይ (ናይል) ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለውን ግድብ የግድቡ ግንባታ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እየተቃወሙ ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት የተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድር ያለ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡
ግብጽ ለሶስትዮሽ ድርደሩ ኢትዮጵያን ተጠያቂ ስታደርግ ኢትዮጵያ በበኩሏ ግብጽ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበሩ ውሎች እንዲቀጥሉ ስለምትፈልግ እንዳልተሳካ አሳውቃለች፡፡