በኢትዮጵያ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት በስፋት ጥቅም ላይ ከዋለ የአገር ዉስጥ እድገት 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጨምር ዓለም አቀፍ የሞባይል ግንኙነት ስርዓት ማኅበር አስታውቋል።
ይህም የሚሆነው በፈረንጆች 2030 ከአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ 60 በመቶ ያህሉ የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ ከሆኑ ነው ያለው ማኅበሩ፤ በተጨማሪም 700 ሺሕ ሰዎችን ከአስከፊ ድህነት እንደሚያወጣና የታክስ ገቢን በ300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚጨምር አመላክቷል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ በአንፃራዊነት 99 በመቶ የኔትወርክ ሽፋን ተደራሽነት ቢኖርም፤ የኔትዎርክ ጥራት አስተማማኝ አለመሆን፣ የዲጂታል ስርዓቱ ግንዛቤ ጉድለት፣ የዕምነትና የመረጃ ግላዊነትና ደህንነት ጥያቄ እንዲሁም የግብይቶች በተደጋጋሚ መስተጓጎል የሞባይል ገንዘብ ክፍያን እና አጠቃቀም ላይ እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በ2021 የኤሌክትሪክ ኃይል ያላቸው ኢትዮጵያውያን 51 በመቶው ብቻ በመሆናቸው ኤሌክትሪክም ሃይል አለመኖር ትልቅ ፈተና ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ጎረቤቶቿ ጋር ሲነጻጸር የገንዘብ ክፍያ ሥርዓት ተሳትፎዋ በጣም ዝቅተኛ ነው ተብሏል።
በ2022 በኬኒያ ከ80 በመቶ በላይ፣ በሩዋንዳ 77 በመቶ፣ በኡጋንዳ 66 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሶች የባንክ ወይም የሞባይል ገንዘብ መክፈያ አካውንት እንዳላቸው የተገኘው መረጃ ጠቁሟል።
በአንጻሩ በኢትዮጵያ ምንም እንኳን ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች እና ኢትዮ ቴሌኮም እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በኢትዮጵያ ቢሰጡም፤ በ2022 በወጣው መረጃ መሰረት በአጠቃላይ 9 በመቶ ብቻ የሚሆነው ህዝብ የሞባይል ገንዘብ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ መሆኑ ተነግሯል።
በአሁኑ ሰዓት መንግሥት ለነዳጅ ግዢ በዲጂታል ክፍያዎች ብቻ እንዲከናወን እና የትራፊክ ቅጣቶችን በዲጂታል ሥርዓት እንዲፈጸም ማድረጉም ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የፍጆታ አገልግሎት ውሃ እና መብራትን የሞባይል ባንኪንግ አፕሊኬሽን ንግድ ባንክ እና ቴሌብርን በመጠቀም በቀላሉ ክፍያ እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።