ኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል ግብር የድጅታል ገንዘብ አገልግሎት ለመስጠት ተስማማ

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ የታክስ ክፍያዎችን በኤም-ፔሳ የዲጂታል ስርዓት ለመሰብሰብ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

ስምምነቱ የዲጅታል ፋይናንስ አገልግሎት አቅራቢ በሆነው ኤምፔሳ_ኢትዮጵያ እና የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ መካከል በባህር ዳር ከተማ ተፈርሟል።

ግብር ከፋዮች ከዚህ በኋላ ኤም-ፔሳን በመጠቀም ግብራቸውን ካሉበት ሆነው በዲጂታል አማራጭ በቀላሉ መክፈል ይችላሉ ተብሏል።

ከ477 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ያሉት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ በ2017 የግብር ዘመን 67 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም ክልሉ 100.37 ቢሊየን ብር የመሰብሰብ እቅድ ያለው ሲሆን ከዚህ ውስጥ እስካሁን 60 በመቶ የሚሆነውን ሰብስቧል ብለዋል።

የታቀደውን ገቢ መሰብሰብ የሚቻለው በዲጂታል አማራጭ በመታገዝ ግብርን በቀላሉና በቀለጠፈ መንገድ መሰብሰብ ሲቻል ነው ብለዋል የቢሮ ሃላፊው።

ከኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ ጋር ዛሬ የተፈረመው ስምምነትም ይህንን የማሳካቱን ጉዞ የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚህ የጋራ ስምምነት በአማራ ክልል የሚገኙ ግብር ከፋዮች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን እና ምቹ የታክስ ክፍያዎችን ባሉበት ሆነው በኤም-ፔሳ በኩል መፈጸም ይችላሉ ብለዋል።

የኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ጌታቸው መንግስቴ፣ ኤም ፔሳ የፋይናንስ ስርዓትን ለማገዝ የሚያስችለውን ስምምነት ከመንግስት ባለ በጀት ተቋማት ጋር ሲፈፅም የአሁኑ የመጀመሪያው መሆኑን ተናግረዋል።

እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ብዙ ሂደትን ማለፍ ነበረብን ብለዋል አቶ ጌታቸው።

የገንዘብ ሚኒስቴር ያፀደቀው አዲስ መመሪያ፣ በብሔራዊ ባንክ እውቅና ያላቸው የፋናንስ አቀላጣፊ ተቋማት ከመንግስት ባለ በጀት ተቋማት ጋርም መስራት እንዲችሉ ይፈቅዳል፤ የመንግስት ተቋማት ለዚህ ዝግጁ መሆን አለባቸው ይላል ብለዋል።

ይህም እንደ ኤም-ፔሳ ያሉት ተቋማት ስራቸውን ወደ መንግስት ተቋማትም እንዲያሰፉ እድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኤም-ፔሳ ኢትዮጵያ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አካል ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ የራሱ ህጋዊ ሰውነት ኖሮት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ሰዓትም በዚሁ የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ከውሃና መብራት ክፍያ ጀምሮ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቲኬት ክፍያ፣ገንዘብ ወጪና ገቢ ማድረግ ያሉ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑ ተወርቷል።

ተቋሙ በሶስት ወራት ውስጥ ሲም ካርዳቸውን የተጠቀሙ ደንበኞቹን የ90 ቀናት ንቁ ደንበኞች ብሎ የሚመዘግብ ሲሆን የዲጂታል ፋይናንስ ንቁ ደንበኞቹ ቁጥርም አምስት ሚሊየን መሻገሩን ተናግሯል።

የሳፋሪኮም የቴሌኮም ደንበኞቹ ቁጥርም ከ12 ሚሊየን በላይ ደርሷል ተብሏል።
በመላው ኢትዮጵያ የአገልግሎት ተደራሽነቴን አስፍቻለው ያለው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በመላው ሀገሪቱ 3500 የኔትዎርክ ማማዎችን እስካሁን ዘርግቻለውም ብሏል።

መንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም የመንግስት ተቋማት አገልግሎታቸውን በዚሁ በኩል እንዲያፋጥኑ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በቅርቡ የኢትዮጵያ ቴሌኮም ገበያን የተቀላቀለው ሳፋሪኮም ከባድ አድርጎበት ቆይቷል፡፡

የዓለም ባንክ ባሳለፍነው መስከረም ባወጣው ሪፖርት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ባልሆነ ውድድር እየተፈተነ መሆኑን ገልጾ ኢትዮጵያ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ የተቋማቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዓለም ባንክ ሪፖርትን እንደማይቀበሉ እና በጫና የቴሌኮም አገልግሎት ታሪፍ ማስተካከያ እንድናደርግ ተገደናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ለደንበኞቹ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በዝቅተኛ ታሪፍ በማቅረቡ ምክንያት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጉን በተደጋጋሚ ሲናገር ቆይቷል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *