የአፍሪካ-ጣሊያን መሪዎች ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

ሁለተኛው የአፍሪካ-ጣሊያን መሪዎች ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ውጭ በአፍሪካ ምድር በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

ይህ ጉባኤ የጣሊያንና አፍሪካ ግንኙነት በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ ትብብሮች ይበልጥ እንዲጠናከር የሚያደርግ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም አህጉሪቱን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማስተሳሰር ያላትን የዲፕሎማሲ አቅም በተግባር ያሳየችበት መድረክ ሆኗል።

በጉባኤው ላይ የሀገራት መሪዎች እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ታሪካዊው ስብሰባ በፈረንጆቹ 2024 በሮም የቀረበውን የጣሊያን “የማቲ ዕቅድ” (Mattei Plan) አፈጻጸም የሚገመግም ሲሆን፣ በተለይም በሀይል ልማት፣ በግብርና፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች ላይ ያተኮረ ሰፊ ምክክር ያደርጋል።

የመንግሥት ኮምኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በትናንትናው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ተስፋሁን በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ 39ኛውን የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ እና የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤን በጋራ ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቃ እንግዶችን በመቀበል ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ታዳሚዎችን በላቀ ሁኔታ ለማስተናገድ የቪዛ፣ የጉምሩክ እና የሚዲያ ፈቃድ አገልግሎቶች በኦንላይን ፖርታል አማካኝነት እንዲሰጡ መደረጉን ሚኒስትር ደኤታው ጠቁመዋል።

ለዚህ ስኬት ከ35 በላይ የፌዴራል ተቋማት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸው ታውቋል።

አቶ ተስፋሁን በጉባኤው ወቅት በሚፈጠሩ መጠነኛ የመንገድ መስተጓጎሎች የከተማዋ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ትዕግሥት እንዲያደርጉም አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ አስተናጋጅነት እየተካሄዱ ባሉት የአፍሪካ-ጣልያን እና የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከ14 ሺህ በላይ እንግዶች በመሳተፍ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል።

የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በዚሁ በአፍሪካ-ጣልያን ጉባኤ ላይ ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል።

ነገ ቅዳሜ እና እሁድ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ የሚካሄድ ሲሆን የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለዚሁ ጉባኤ አዲስ አበባ በመግባት ላይ ናቸው።

እስካሁን የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የዛምቢያ ፕሬዝዳንት ሂቼልማ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር፣ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ የሩዋንዳ ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ አበባ ገብተዋል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *