ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ ልትገነባ መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዩኒቨርሲቲ ልትገነባ መሆኑንና ለዚህም የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ”የምሁራን ሚና ለሀገር ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደተናገሩት፤ በቴክኖሎጂው ዘርፍ መሽቀዳደም የግድ ይላል ብለዋል።

አሁን ላይ በዓለማችን አንድ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሚገነባው ደግሞ የዓለማችን ሁለተኛው ይሆናል ማለታቸውንም ጋዜጣ ፕላስ ዘግቧል።

ዩኒቨርሲቲው በቁጥር ጥቂት ነገር ግን ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን 1 ሺህ ተመራቂዎች ለማፍራት ያለመ መሆኑን ዐቢይ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ለሁሉም የአፍሪካ ሀገራት የ100 ተማሪዎች ኮታ በመስጠት ከእያንዳንዱ ሀገር ሁለት ሁለት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንዲሰለጥኑ ይደረጋል።

ከኢትዮጵያ ደግሞ ሁለት በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች በከፍተኛ ውድድር ተመርጠው እንዲገቡ በማድረግ፣ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ተግባራዊ እውቀት ያለው የሰው ኃይል ለመፍጠር በትኩረት እንደሚሠራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዝርዝር አመልክተዋል።

የግንባታው መጀመር ኢትዮጵያ በዘመናዊው የቴክኖሎጂ ምህዳር ውስጥ ያላትን ሚና ከፍ የሚያደርግ መሆኑም በዕለቱ ተገልጿል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *