ብሔራዊ ባንክ እንዳስታወቀው በአንድ አመት ውስጥ በጂታል ክፍያ ስርአት 18 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ዝውውር ተፈጽሟል።
በኢትዮጵያ ዲጂታል ክፍያ ኮንፈረንስ 2.0. ላይ ለአምስት አመት የሚቆይ (2026-30) የብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ በብሔራዊ ባንክ ይፋ ሆኗል።
የመጀመሪያው የ2021-24 ብሄራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ላይ ህግ ማውጣት፣ተቋማት አገልግሎቱን እንዲሰጡ ማስቻልና ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ እንዲሁም መሠረተ ልማት ዝርጋታ መከናወናቸው ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ስርአት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ዳምጠው ለቅዳሜ ገበያ እንደገለጹት በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ትልቁ ሚና የገንዘብ ዝውውር ፈጣን ቀልጣፋ ወጪ ቆጣቢ መሆን አለበት።
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ የዲጂታል የክፍያ ስርአትን ማዘመን እና ለዚያ የሚያበቃ የድጅታል መሰረተ ልማት ግንባታ ጉልህ ሚና ይጫወታል።
ባለፈው አንድ አመት በዲጂታል ክፍያ ስርአት 18 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር መዘዋወሩን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚው የሚንቀሳቀሰው በጥሬ ብር ነው ያሉት አቶ ሰለሞን ይህን መለወጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በቀጣይ አምስት አመት 75 በመቶ ክፍያ ስርዓት በዲጂታል እንዲያልፍ፣ አሁን ላይ በወንዶችና በሴቶችን የዲጂታል ክፍያ ስርአት አጠቃቀም 24 በመቶ ልዩነት ሲኖረው በቀጣይ አምስት አመት የሴቶችን ተጠቃሚ ቁጥር በማሳደግ ልዩነቱን ወደ 3 በመቶ ለማውረድ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ያለፈውን አምስት አመት ግምገማን ውጤት መሰረት በማድረግ በቀጣይ አምስት አመት ኢትዮጵያውያን የሚያገናኝ የታመነ፣ የተቀናጀ እና ተደራሽ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ስነ-ምህዳር እውን ለማድረግ ትኩረት እንደሚሰጥም ተገልጿል።