ከ100 ቢሊየን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል የተጠረጠሩ የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶችና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ገልጿል።
መ/ቤቱ ፤ በቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶችና ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር በሚባሉ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተባባሪ ተቋማት ዙሪያ ጥናትና ክትትል ሲከናወን መቆየቱን አመልክቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ፈቃድ ያላቸውና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በገቡት ውል መሰረት ባለመስራት፣ በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው በመገኘታቸው ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው፣
ምንም አይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በስፖርት አወራራጅነት ተሰማርተው የነበሩ አካላት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ትስስር አማካይነት በሕገ-ወጥ ድርጊት ተሰማርተው ተገኝተዋል ተብሏል።
ከፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ትብብር 24 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አሳውቋል ሲል ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።
በተለይ በሕጋዊነት ሽፋን ፈቃድ ያወጡት ድርጅቶች ላይ ክትትል ለማድረግ ሙከራ በተደረገበት ወቅት ሁሉም ፈቃድ ሲያወጡ ይዘውት ከነበረው ቢሮ መልቀቃቸውና አድራሻቸውን መሰወራቸው መረጋገጡን ገልጿል።
የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ስርዓቶችን ከሚያሳልጡላቸው የሀገር ውስጥ የክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር በአጠቃላይ ሲያንቀሳቅሱት ከነበረው የገንዘብ መጠን መንግሥት በተለያዩ የገቢ አማራጮች ማግኘት የነበረበትን 100 ቢሊየን ብር በላይ መሰወራቸው እንደተደረሰበት አመላክቷል፡፡
የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ በተለያዩ የገንዘብ ክፍያ ስርዓቶች አማካይነት የሚሰበስቡትንና የሚያዘዋውሩትን የገንዘብ መጠን ያማከለ ግብር አለመክፈላቸው እንደተደረሰበት ጠቁሟል።
እንዲሁም በክሪፕቶከረንሲ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ገንዘብ ማስተላላፊያ አማራጮች አማካኝነት የሚያገኙትን ገቢ በውጭ ምንዛሪ በመቀየር ሲሰውሩና ከሀገር እንዲወጣ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጷል።
ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር የሚባሉት የሀገር ውስጥ የገንዘብ ክፍያ ስርዓት አቅራቢ ተቋማቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም፤ የደንበኛን ምስጢር መጠበቅ የሚል ሙያዊ አሠራርን እንደ ሽፋን ተጠቅመው የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን የገንዘብ መጠን ከሚመለከታቸው የመንግሥት አስፈፃሚ ተቋማት በመደበቅ ወይም አሳንሶ በማቅረብ በግብር ስወራ እንዲሁም ከፍተኛ የሀገር ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው አመልክቷል።
የተለያዩ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ገለሠቦች ጭምር ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ሀገር ውስጥ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችው ውክልና በመስጠት ሕገ-ወጥ ድርጊቱን ሲፈጸሙ መቆየታቸው እንዲሁም ውጭ ሀገር የበለጸጉ ሶፍትዌሮች ጥቅም ላይ መዋላቸውና ድርጅቶቹ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው መሆኑ ወንጀሉን ውስብስብና ለቁጥጥር አስቸጋሪ አድርጎት እንደቆየ ገልጿል።
ምንም እንኳን ጉዳዩ ውስብስብ ቢሆንም የደኅንነት ተቋሙ ከሌሎች የመረጃና የጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር ተጠርጣሪዎቹን መያዙን አመልክቷል።
ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስለ ተጠርጣሪዎች ማንነት እንዲሁም ስለ ቤቲንግ ድርጅቶቹ (ስም) ፣ በህገወጥ ስራ ተሰማርተው የተገኙት የትኞቹ የፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ድርጅቶች እንደሆኑ ለጊዜው በይፋ ያለው ነገር የለም።