የ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24 እንዲሆን ቀረበ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ በመጪው ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለማድረግ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

የምርጫ ውጤት ለህዝብ ማሳወቂያ ቀን ደግሞ ሰኔ 3 ቀን እንደሚሆንም ቦርዱ አስታውቋል።

ሰባተኛው ሀገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ የሚገኘው ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ከ60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በተሳተፉበት በዚህ ውይይት ላይ በምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ የጦፈ ውይይት መደረጉ ተገልጿል።

መገናኛ ብዙሃን ባልተገኙበት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፤ ምርጫ ቦርድ የሰባተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳን ለፓርቲዎች ለውይይት አቅርቧል።

ለውይይት በቀረበው የጊዜ ሰሌዳው መሰረትም ህዳር ወር ውስጥ በምርጫ መወዳደር የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የግል ዕጩዎች ይመዘገባሉ ተብሏል።

የምርጫ አስፈጻሚዎችን ዝርዝር ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለህዝብ ይፋ ማድረግ፤ ህዳር 19 ተጀምሮ በጥር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ለማጠናቀቅ ታስቧል።

የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ምዝገባ ደግሞ ከታህሳስ መጀመሪያ እስከ ጥር የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ እንዲመዘገቡ በእቅዱ ላይ ተጠቅሷል።

እንዲሁም የምረጡኝ ቅስቀሳ ከታህሳስ 10 እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ እንዲከወን የታቀደ ሲሆን ከግንቦት 20 እስከ 23 ያሉት ሶስት ቀናት ደግሞ ቅስቀሳ የማይደረግባቸው ወይም የጽሞና ጊዜ እንዲሆኑ በሚል ቦርዱ ማሳወቁን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።

ግንቦት 24 ቀን መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ቀን ይሆናል የተባለ ሲሆ ከግንቦት 25 ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት ደግሞ ጊዜያዊ ውጤት ይፋ እንደሚደረግ ተገልጿል።

በውይይቱ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ምርጫ ለማድረግ አመቺ እንዳልሆነ እና የሰላም ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል ተብሏል።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *