ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ከኤርትራ መረከቧ አይቀሬ መሆኑን ገለጸች

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ኮሞዶር ተገኝ ለታ እንዳሉት የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ መመለስ ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሰላምና መረጋጋት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክትል አዛዡ ይህን የተናገሩት ጥቅምት 8 ቀን 2018 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ በመከላከያ ዋር ኮሌጅና በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትብብር “የሁለቱ የውሃ ሥርዓቶችና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ነፃነት፣ የዓባይና የቀይ ባሕር ትስስር እና የአፋር ክልልን ስትራቴጂካዊ ሚና መዳሰስ” በሚል ርዕስ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ምክትል አዛዥ ኮሞዶር ተገኝ ለታ የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በሀገሪቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ሊኖረው የሚችለው ኢኮኖሚዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ መዘዝን መረዳት ተገቢ መሆኑንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

“የወደብ ጉዳይ መንግስታዊ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል” ያሉት የባህር ኃይል ምክትል አዛዡ፤ በቀይ ባሕር ቀጣና እየታዩ ናቸው ያሏቸው ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጦች  ኢትዮጵያ ከቅርብ ባሉት ነገር ግን በውል ካልጠቀሱት ጊዜ ወዲህ በቀይ ባህር ላይ ያላት ጥያቄ ቀዳማዊ ብሔራዊ አጀንዳ ለማድረጓ ገፊ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ያለው የሎጂስቲክስ ፍላጎት ለኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄው መነሳት አንደኛው ምክንያት መሆኑንም አመላክተዋል።

እንደምክትል አዛዡ ገለጻ፤ የባሕር በር ያስፈለገበትን ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ያሏቸው ነገር ግን በስም ያልጠቀሷቸው ሀገራት በቀጣናው የጦር ሰፈር መገንባታቸው ነው።

“በመሆኑም የጦር ሰፈሮች በቀጣናው መኖራቸው ይዟቸው የሚመጡ ችግሮችን ቀድሞ በመተንበይ፣ በመዘጋጀት፣ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ያተኮረ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

የወደቡ ጉዳይ ዕልባት አለማግኘት ከቀጠለ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አስተዋጽዖ ማድረጉ እንደማይቀርም አዛዡ አክለዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ የወደብ ጥያቄው ካልተመለሰ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል።

በሰሜናዊ ሕንድ ውቅያኖስ እና ቀይ ባህር ላይ የሚታዩ ውንብድናዎችንና ግጭቶችን ለመከላከል ጠንካራ የባህር ኃይል አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ስለመሆኑም ምክትል አዛዡ ተናግረዋል።

የባሕር በር አስፈላጊነትን፣ ኢትዮጵያ የባሕር በሯን በግፍ መነጠቋን እንዲሁም መመለሱ አይቀሬ መሆኑን ሲናገሩ ምክትል አዛዡ የመጀመሪያው አይደሉም።

በመከላከያ ሚኒስቴር የውጪ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተሾመ ገመቹ የባህር በር እየጠየቅን ያለነው “ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን አይደለም” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ለዚህም አራት ምክንያቶችን የጠቀሱ ሲሆን እነዚህም ኢትዮጵያ ከአሰብ ጋር ያላት ታሪካዊ ትስስር፣ መልካም ምድራዊ ቅርበት፣ የህልውና ጥያቄ እና የጸጥታ ስጋቶች መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

ሌሎች ወታደራዊ መኮንኖችም ተመሰሳሳይ አስተያየት ሲያንጸባርቁ መክረማቸውም አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ቀጠና ሆን ተብሎ እንድርቅ እና እንድታፈን ተደርጌያለሁ በሚል የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ መንግሥት ዳግም የባህር በር ለማግኘት በጥረት ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው የሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የቀይ ባህር ጉዳይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ የሚነሱ የወደብ ጥያቄዎች የሀገርን ሉዓላዊነት እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የማያከብሩ ናቸው በሚል በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *