አየር መንገዱ ከ10 ዓመት በኋላ ዓመታዊ ገቢውን 25 ቢሊዮን ዶላር የማድረስ እቅድ እንዳለው አስታውቋል።
ከ10 ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ 25 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ፡፡
አቶ መስፍን እንደገለጹት አየር መንገዱ እ.ኤ.አ በ2035 ላይ 209 ዓለም አቀፍ እና 31 የሀገር ውስጥ መዳረሻዎች፣ 271 አውሮፕላኖች እንደሚኖሩትም ጠቅሰዋል፡፡
አየር መንገዱ 67 ነጥበ 2 ሚሊዮን መንገደኞችንም በማጓጓዝ ከ10 ዓመት በኋላ ገቢውንም 25 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም አዳዲስ መዳረሻዎችን በማስፋት ትስስሩን ይበልጥ ማጠናከር እና አዳዲስ መዳረሻዎችን መክፈት የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም አሁን በረራ ከሚደረግባቸው አምስቱ ክፍለ አኅጉሮች ተጨማሪ አውስትራሊያንም የሚጨመር መሆኑን ጠቅሰው፤ በብዙ ሀገሮች አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እስከ አራት ጊዜ በረራ ለማድረግ መታቀዱንም ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡
ያረጁትን አውሮፕላኖችን በመለወጥ አዳዲስ ዘመናዊ አውሮፕላኖች የሚመጡ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ጥሩ ሥነምግባር እና ተነሳሽነት ያለው ሠራተኛ መገኘት መቀጠል አለበት ያሉት አቶ መስፍን፤ በየዓመቱ 300 ፓይለት ለማሰልጠን እቅድ መያዙንም አስታውቀዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በኋላ ማለትም በ2029 ሙሉ በሙሉ ወደ አዲሱ ኤርፖርት የሚገባ መሆኑን ገልጸው፤ አዲሱ ኤርፖርት በጥራትም በስፋትም ከአፍሪካ አንደኛ በመሆን የአፍሪካን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ከሌላው ዓለም ደረጃ ላይ እናደርሳለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት 100 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገድ የሚያስችል አዲስ ኤርፖርት በመገንባት ላይ ይገኛል።
10 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይፈጃል የተባለው አዲሱ ኤርፖርት በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።