ኢትዮጵያ ኢንተርኔትን በተደጋጋሚ በመዝጋትና የኢንተርኔትን ነጸነት በመገደብ ከአፍሪካ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን በብሉምስበሪ አሳታሚ ላይ የታተመ አንድ የጥናት መጽሐፍ አመላከተ።
“የኢንተርኔት መዘጋት በአፍሪካ” በሚል ርእስ በፊሊሽያ አንቶኒዮ እና ቶኒ ሮበርትስ የተጠናውና መቀመጫውን በብሪታንያ ባደረገው ብሉምስበሪ አሳታሚ ድርጅት ላይ በመጸሐፍ መልክ ታትሞ የወጣው ጥናት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2024 በአህጉረ አፍሪካ በሀገራት የተፈጸመውን የኢንተርኔት መዘጋት ገምግሟል።
በዚህም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2016 እስከ 2024 ባሉት በለፉት ዘጠኝ ዓመታት 193 የኢንተርኔት መዘጋት በአፍሪካ አህጉር መመዝገቡን ገልጿል።
በተጠቀሱት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በተፈጸሙ የኢንተርኔት መዘጋት ድግግሞሽ መጠኖች ሀገራትን በደረጃ ያስቀመጠው ጥናቱ ኢትዮጵያን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሰላሳ ጊዜ ኢንትርኔት የዘጋች በሚል ከ55ቱ የአፍሪካ ሀገራት በአንደኛ ደረጃ አስቀምጧታል።
በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች የምትገኘው ጎረቤት ሀገር ሱዳን በተጠቀሱት ዓመታት ውስጥ 21 ጊዜ ኢንተርኔትን በመዝጋት በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።
እንዲሁም ባለፉት ዓመታት በሰላም እጦትና በግጭት ውስጥ ያለችው ሰሜን አፍሪካዊቷ አልጀሪያ ደግሞ 14 ጊዜ ኢንተርኔትን በመዝጋት በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአፍሪካ የተፈጸመው የኢንተርኔት መዘጋት ሁኔታና የድግግሞሽ መጠኑ ከሀገር ሀገር ከፍተኛ ልዩነት የሚታይበት መሆኑንም የጥናቱ ውጤት አመላክቷል።
በዚህም ምንም እንኳዓን በብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የኢንተርኔት መዘጋት የነበረ መሆኑን የጠቆመው ጥናቱ፤ በዚያው ልክ ደግሞ በ14 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ አንድም የኢንተርኔት መዘጋት አልተመዘገበም።
በሌሎች 14 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ደግሞ የኢንተርኔት መዘጋት የገጠመው አንድ፣ አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን አስታውሷል።
በአህጉሪቱ የተፈጸመው የኢንተርኔት መዘጋት ክስተት በመጠንና በድግግሞሽ ብቻ ሳይሆን ለድርጊቱ መፈጸም መንስኤ በሆኑ ገፊ ምክንያቶች ጭምርም ሰፊ ልዩነት የሚታይበት መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
የመንግሥታት ሕዝባዊ አመጽን መፍራት፣ በሀገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ግጭቶችና ጦርነቶች፥ ምርጫን ተከትለው ሊቀሰቀሱ የሚችሉ አመጾች፥ የፈተና መሰረቅንና መጭበርበርን ለማስቀረትና የፖለቲካ ተቃውሞን ለማፈን የሚወሰዱ ሴንሰርሽፖች ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአህጉሪቱ ለተፈጸሙ የኢንተርኔት መዘጋትና በኢንተርኔት ነጻነት ላይ ለተፈጸሙ ገደቦች ዋነኛ መንስኤ ሆነው መለየታቸውንም ጥናቱ ገልጿል።
ኢትዮጵያን በተመለከተም የኢንተርኔት መዘጋት በተለይም በግጭትና በጦርነት ወቅት ሊኖረው የሚችለው ውጤትና በዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖና በጥናቱ ተካቷል።
የኢንተርኔት መዘጋቱ የዜጎችን የመረጃ ነጻነት ከመገደቡ ባለፈ መንግሥት እና ዜጎች ገቢያቸው እንዲቀንስ ማድረጉም ተገልጿል።