በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ከተፈተኑ 586 ሺህ ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 49 ሺህ ገደማ ህሉ ብቻ ናቸው ተብሏል።
በ2017 የትምህርት ዘመን የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 585 ሺህ 882 ተማሪዎች መካከል 48 ሺህ 929 ማለፋቸውን የትምህርት ሚኒስትር አስታውቋል።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የፈተና ውጤቱን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት ፈተና ከወሰዱ 585 ሺህ 882 ተማሪዎች መካከል 48 ሺህ 929 ከ50 በመቶ በላይ ያስመዘገቡ በመሆናቸው ወደ ዩንቨርስቲ ይገባሉ ብለዋል።
ፈተናቸውን ከወሰዱ አጠቃላይ ተማሪዎች መካከል 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ካስመዘገቡ የማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች 5.2 በመቶ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ደግሞ 11.4 በመቶ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።
እንደ ፕሮፌሰሩ ገለፃ በዘንድሮው ዓመት የ68 ሺህ ተማሪዎች የፈተና ውጤት አንድ በአንድ የማረም ስራ በመከናወኑ ውጤት ይፋ ማድረጊያ ጊዜው ዘግይቷል።
በሌላ አባባል ከተፈታኞች መካከል 536 ሺሕ 953 ወይንም 91 ነጥብ 6 የሚሆኑት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ማጠናቀቂያ ፈተናውን ያላለፉ ሲሆን የሬሚዲያል ፕሮግራም እንደሚኖር ተገልጿል።
1 ሺህ 249 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም የተባለ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነጻጸር 114 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በማሳለፍ መሻሻል አሳይተዋል ተብሏል።
እንዲሁም ያስፈተኗቸው ሁሉንም ተማሪዎች ያሳለፉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ 50 ትምህርት ቤቶች እንደሆኑም ሚኒስትሩ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
በዘንድሮው የተመዘገበው ውጤት ራሳችንን የምንፈትሽበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የፈተና ስርቆት ምጣኔው መቀነስ የተቻለ ሲሆን፤ 120 ተማሪዎች ሲኮርጁ ተገኝተው ውጤታቸው መሰረዙን ተናግረዋል።
የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑ የገለፁት ሚኒስትሩ፤ በዚህም ባለፈው ዓመት 36 ሺህ 409 ተማሪዎች የነበረ ቢሆንም በዘንድሮው ዓመት 48 ሺህ 929 ተማሪዎች ማለፋቸውንም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ፣ ሀረሪ እና አማራ ክልል በአንጻራዊነት ብዙ ተማሪዎች ያለፉባቸው ክልሎች ሲሆኑ አዲስ አበባ ከተማ 888 ተማሪዎች ከ500 በላይ ውጤት በማስመዝገብ ከሁሉም ክልሎች በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 የዶዶላ ኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት ተፈታኝ 591 በማምጣት ከፍተኛው ውጤት ነው ተብሏል።
ከሴት ደግሞ የአዲስ አበባው ብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት 579 ማምጣቷ ተገልጿል።
እንዲሁም በማህበራዊ ሳይንስ 562 ወንድ ከአምቦ ቦርዲግ ትምህርት ቤት ከሴት ደግሞ 548 የአዲስ አበባው ሴንት ጆሴፍ ትምህርት ቤት ተማሪ አስመዝግባለች ተብሏል።