ንግድ ባንክ ለዲያስፖራው ማኀበረሰብ 50 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት አዘጋጅቼ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቋል።
የባንኩ የብድር አገልግሎቱ ለኢንቨስትመንት፣ ለመኖሪያ ቤትና አውቶሞቢል ግዥ የቀረበ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚደንት አቶ አቤ ሳኖ ሰሞኑን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ፕሬዚደንቱ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በአገር ውስጥ ለሚያካሄዱት የቢዝነስ እንቅስቃሴ፣ ለመኖሪያ ቤትና መሰል ፍላጎቶች የ50 ቢሊዮን ብር የብድር አገልገሎት ተመቻችቷል ብለዋል፡፡
የብድር አገልግሎቱ በተያዘው የ2024/25 በጀት ዓመት ተፈጻሚ እንደሚሆንም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ባንኩ አገልግሎቱን ለማግኘት ጥያቄ ለሚያቀርቡ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ቀልጣፋና ምቹ አሰራር እንደሚተገብርም አቶ አቤ አስታውቀዋል፡፡
ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመስከረም ወር ጀምሮ የአገልግሎት ክፍያዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች መረጃ ከሆነ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ሲሆን አብዛኞቹ በመካከለኛው ምስራቅ፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ሀገራት ይኖራሉ።
ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ይኖርባቸዋል።
የብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ማሞ ምህረቱ ከአንድ ወር በፊት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት ውስጥ ከሬሚታንስ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሜሪካ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ከተሞች ሆነው ህገወጥ የሬሚታንስ ገንዘብ ዝውውርን ይፈጽማሉ ያለቻቸውን ድርጅቶች ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መግለጫ በህገወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ ያሉ አካላት ከድርጊታቸው ካልታቀቡ አካውንት ከመዝጋት ጀምሮ ገንዘባቸው እንደሚወረስም ተገልጿል።