ኢትዮጵያ በውጭ ሀገራት የሚሰማሩ ስራ ተቋራጭ ድርጅቶችን የማሳደግ እቅድ እንዳላት ተገለጸ

10 የስራ ተቋራጭ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ውጪ ውጪ ባሉ ሀገራት መሰማራታቸውን የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚንስቴር አስታውቋል

ሚንስቴሩ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተሰማሩ የኢትዮጵያ ስራ ተቋራጭ ድርጅቶችን ቁጥር 20 የማድረስ እቅድ መያዙን ገልጿል።

የሀገራቱን አስፈላጊ መስፈርት አሟልተውና በጨረታ አሸንፈው በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ የሚሳተፉ ተቋራጮችን ቁጥር ወደ 20 ከፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሚንስትሩ ሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢትዮጵያ በዴቻ፤ “ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የግንባታ ሥራ ለማከናወን ፈቃድ ተሰጥቷቸው በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የኮንትራት ሥራዎችን ወስደው በግንባታ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የግንባታ ስራ ተቋራጮች ቁጥር ከ10 አይበልጥም” ብለዋል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴሩ ይህን የግንባታ ሥራ ተቋራጮች ቁጥር ወደ 20 ከፍ ለማድረግ የተቋማቱን አቅም የማሳደግ ሥራዎች በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ለአሐዱ ተናግረዋል።

በኮንስትራክሽን ኢንደስትሪው ላይ ሥር-ነቀል ለውጥ በማምጣት እና ዘርፉን ከሀገር ውስጥ ባሻገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን፤ ችግርችን መፍታት፣ ምቹ ምህዳር መፍጠር፣ የላቀ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንደሚጠቅ ያነሱት አቶ ኢትዮጵያ፤ “በዘርፉ ላይ እየታዩ ያሉ ለውጦች አበረታች ቢሆኑም በቂ ናቸው ማለት አይቻልም” ብለዋል።

የሀገር ውስጥ ሥራ ተቋራጮች ከሚነሱባቸው እንከኖች መካከል የግንባታ ጥራት፣ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ አለማጠናቀቅ፣ የክህሎት ማነስ፣ የበጀት እጥረት፣ ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንደሆነ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ስራ ተቋራጮች የበጀት ዕጥረት፣ ከውጭ ሀገራት በመጡ በተለይም በቻይና ስራ ተቋራጮች ከፍተኛ ውድድር እየገጠመው ሲሆን የጸጥታ ችግሮችም ዋነኛ ፈተና እንደሆነበት የኮንስትራክሽን እና ስራ ተቋራጮች ማህበር ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር የውጪ የግንባታ ስራ ተቋራጮች ከ 2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ለሚያወጡ ስራዎች ብቻ እንዲጫረቱ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የውጪ ሃገራት ስራ ተቋራጮች በስፋት በኢትዮጵያ ውስጥ በመሰማራታቸው የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከገበያ ውጪ እየሆኑ መሆኑንም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ግርማ ሀብተማርያም ተናግረዋል።

ሕጉ የውጪ ተቋራጮች ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ለሆነ ስራ ብቻ መጫረት አለባቸው ቢልም ይህ ተግባራዊ እየሆነ እንዳልሆነና ከ50 ሚሊዮን ብር ያነሰ ስራ ላይ ሳይቀር የውጭ ኩባንያዎች በተለይም ቻይናዊን እየተጫረቱ እንደሚገኙ ሰምተናል።

የውጪ ተቋራጮች በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ በስፋት ቅድሚያ የሚያገኙበት አስራር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው ፕሬዝዳንቱ አፅእኖት የሰጡት።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በአዲስ መልክ እየተሻሻለ እንደሚገኝ የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር በቅርቡ ማስታወቁ አይዘነጋም።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *