የኬንያው ኪሲቢ ባንክ የኢትዮጵያን ባንክ 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ንግግር ጀመረ

ብሔራዊ ባንክ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ ህግ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

ይህንን ተከትሎም የኬንያው  ኬሲቢ ግሩፕ በኢትዮጵያ ባንክ ኢንቨስትመንት ለመስራት በንግግር ላይ መሆኑን ቢዝነስ ዴይሊ ዘግቧል፡፡

ባንኩ በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ በኢትዮጵያ የሚገኝን አንድ ባንክ 40 ከመቶ ድርሻን ለመግዛት ንግግር በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል።

ይሁንና ኬሲቢ ከየትኛው የኢትዮጵያ ባንክ ጋር ንግግር እንደጀመረ በዘገባው ላይ አልተገለፀም።

ያም ሆነ ይህ የኬንያ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሰፊ የባንክ ስራዎችን በመስራት በኢትዮጵያ ተመራጭ ባንክ ለመሆን እቅድ ይዟል።

ብሔራዊ ባንክ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣዉ መግለጫ መመሪያው የውጭ ተዋናዮች የባንክ ዘርፉን እንዲቀላቀሉባቸው በርካታ መንገዶችን ያቀርባል፤ ከእነዚህም መካከል ቅርንጫፍ ባንኮችን፣ የውጭ ባንክ ቅርንጫፎችን ወይም የወኪል ቢሮዎችን ማቋቋም ይገኙበታል።

ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን የባንክ ዘርፍ ለውጭ ተሳትፎ ክፍት መሆኑን የገለፀ ሲሆን የውጭ ባንኮች እና ባለሀብቶችም ማመልከቻዎቻቸውን ከዛሬ ጀምሮ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቋል።

ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ዓመት በፊት በባንክ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው የውጭ ባለሀብቶች አምስት የሚደርሱ የባንክ ፈቃድ ለመስጠት እንደታቀደ ገልጾ ነበር፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ በኢትዮጵያ በባንክ ዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ የውጭ ባለሀብቶች የባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ በወቅቱ ገመናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢ ማሞ ምህረቱ ከሶስት ወር በፊት በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም በተካሄደ የባንክ ኤክስፖ ላይ ባደረጉት ንግግር የ2025 ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ ብለው ነበር።

ከኬንያው ኬሲቢ ባንክ በተጨማሪ የደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽ እና ናይጀሪያ ባንኮች በኢትዮጵያ ባንክ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡

የናይጀሪያው ኮሬ የባንክ ቴክኖሎጂ ኩባንያ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረ ሲሆን ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር የክፍያ ቴክኖሎጂዎች፣ ሞባይል ባንኪንግ እና መሰል ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ከአንድ ወር በፊትም አኮፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ በኮሬ ቴክኖሎጂስ የለማውን የባንኪንግ ቴክኖሎጂ ተረክቦ ስራ ጀምሯል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *