የፌደራል ዋና ኦዲተር የመንግስት ተቋማት የ2016 በጀት ዓመት የበጀት ኦዲት አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው 17 የመንግስት ተቋማት በጡረታ፣ በሞትና በሌሎች ምክንያት ከሥራ ለለቀቁ ሰራተኞች 408,462 ብር ያላግባብ ደመወዝ ከፍለው ተገኝተዋል ተብሏል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በልዩ ሁኔታ ካልተፈቀደ በስተቀር የሰራተኞች ቅጥር፣ የደረጃ ዕድገትና ዝውውር እንዳይፈጸም ቢከለክልም በስምንት መስሪያ ቤቶችና በአንድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በጠቅላላው 24,073,003 ብር የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን ሳያስፈቅዱ በቋሚ የሥራ መደቦች ላይ ሰራተኞችን በኮንትራት በመቅጠር ክፍያ ፈጽመዋልም ተብሏል፡፡
ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽንን ሳያስፈቅዱ የኮንትራት ቅጥር ከፈጸሙት ተቋማት መካከል የቅደስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ፣ ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣የአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋነኞቹ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በ2015 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት በተከናወኑ የኦዲት ሪፖርቶች መሠረት እርምጃ የተወሰደ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ በጠቅላላ እንዲመለስ አስተያየት ከተሰጠበት 20.5 ቢሊዮን ብር እና 23,230 የአሜሪካ ዶላር ውስጥ የተመለሰው የገንዘብ መጠን ሶስት ቢሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ የፌደራል ኦዲት ዋና ኦዲተር አስታውቋል፡፡
የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፣የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች አገልግሎት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በጠቅላላው 37,304,100 ብር የአገልግሎት ገቢ ተመናቸው በሚመለከተው አካል ሳያጸድቁ ገቢ መሰብሰባቸውም ተገልጿል፡፡
እንዲሁም 28 የፌደራል መስሪያ ቤቶችና ሰባት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች 348 ሚሊዮን ብር የፈጸሙት ክፍያ የተሟላ የወጪ ማስረጃ አልቀረበበትም ተብሏል፡፡
የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ከተመዘገቡት መሥሪያ ቤቶች መካከል የጤና ሚኒስቴር ብር ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የቤተ መንግሥት አስተዳድር ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በ70 የፌደራል መስሪያ ቤቶችና በ7 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከ404 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥትን የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ መገኘቱን ዋና ኦዲተር ገልጿል፡፡ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንና አርሲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ከህግ ውጪ ግዢ ከፈጸሙ ተቋማት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ስምንት ተቋማት ደግሞ በጠቅላላው ከ6.5 ሚሊዮን በላይ ብር ዋጋ ያላቸውና ተገዝተዋል የተባሉ ንብረቶች እስካሁን ገቢ እንዳላደረጉ ሲገለጽ የህዝብ እንባ ጠባቂ፣የቤተ መንግሥት አስተዳድርና መቀሌ ዩንቨርሲቲ ደግሞ ግዢውን ፈጽመው እቃዎቹን ገቢ ያላደረጉ ተቋማት ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም በ2016 በጀት ዓመት 20 የፌደራል መስሪያ ቤቶች ከተመደበላቸው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ ሳይጠቀሙበት ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ ማድረጋቸውን ዋና ኦዲተር አስታውቋል።