ከዚህ ቀደም የቡና ላኪነትን የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ይጠየቅ የነረበው የ1.5 ሚሊዮን ብር በ10 እጥፍ እንዲያድግ የተደረገው ዘርፉ በእውቀትና የተሻለ አቅም ባላቸው ሰዎች እንዲያዝ በማስፈለጉ ነው ተብሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት ይጠየቅ የነበረው ካፒታል 1.5 ሚሊየን ብር ነበር፤ ይህ ገንዘብ አሁን በአስር እጥፍ እንዲያግ በኢትዮጵያ ቡና ሻይ ባለስልጣን ማሻሻያ መቅረቡ ተሰምቷል።
የሚጠየቀው ካፒታል አነስተኛ ሆኖ በመቆየቱ አትራፊ ነው በሚል ብቻ ብዙዎች የሚገቡበት ዘርፍ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ናቸው።
ይሄ ደግሞ እዚሁ ሀገር ቤት በአቅራቢ እና ላኪዎች እንዲሁም ላኪዎች እና የውጭ ገዥዎች መካከል ችግሮች እንዲፈጠሩ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
የቡና_ንግድ ሰዎች የተወሰነ ገንዘብ በአንድ አጋጣሚ ስላገኙ ብቻ የሚገቡበት ሊሆን አይገባም የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ ስለ ዋጋው፣ ጥራቱ እና የአዘገጃጀት ሂደቱ ማወቅ ወሳኝ እንደሆነ ያክላሉ።
የነጻ ገበያ መርህ ሁሉም ሰው በእኩልነት ይወዳደር፤ ገበያው በራሱ አላፊውን እና ከወዳቂው ይለያል የሚል እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ግዛት ይሄ ግን በቡና ንግድ ላይ ብዙም እየሰራ አይደለም ብለውናል።
የቡና ላኪነት የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት የሚጠየቅ ማህበር ወይም ግለሰብ ከካፒታሉ በተጨማሪ የአንድ ዓመት የፋይናንስ እንቅስቃሴውን የሚያሳይ በባንክ የተረጋገጠ ሰነድ ማቅረብ እንደሚጠበቅበትም ተጠቅሷል።
የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የወሰደ ቡና ላኪ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ መግባት እንዳለበትም በመመሪያው ሰፍሯል።
ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ወደ ስራ መግባት ካልቻለ ደግሞ ይህንኑ በማስረጃ አስደግፎ ለቡናና ሻይ ባለስልጣን ማቅረብ ይኖርበታል ተብሏል።
ማሻሻያው የሚመለከታቸው ከመከሩበት በኋላ ስራ ላይ እንደሚውል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ተናግሯል።
ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ የምታገኘው ገቢ እየጨመረ ሲሆን ባለፉት 10 ወራት ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። በተያዘው ዓመት ውስጥ ደግሞ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።