በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ክፍያ ሰነድ አውጪ የሆነው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪስ ከኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር አሽከርካሪዎች ካቻን በመጠቀም በቀላሉ የነዳጅ ክፍያን የሚከፍሉበትን አገልግሎት በትናንትናው እለት ይፋ አድርጓል።
አገልግሎቱም ደንበኞች የካቻን መተግበሪያ በመጠቀም ፣ በ“Push USSD Notification” እንዲሁም በQR ኮድ ስካን በማድረግ በቀላሉ የነዳጅ ክፍያን መፈፀም የሚያስችል ሲሆን የካቻ ደንበኛ ያልሆነ ማንኛውምአሽከርካሪ መተግበሪያውን ከፕሌይስቶር ወይም አፕስቶር በማውረድ ከማንኛውም ባንክ ወደ ካቻ ገንዘብ በማስተላለፍ ወዲያውኑ ክፍያ መፈፀም እንደሚያስችል ተገልጿል።
“የዛሬው ምርቃት ካቻ ለማህበረሰባችን ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ፉይናንስ አገልግሎት ለመስጠት ለሚያደርገው ጉዞ አንድ እርምጃ የሚያግዘን ነው”ያሉት የካቻ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብርሀም ጥላሁን “በቀጣይም ካቻ በአሽከርካሪዎች ላይ ያለውን የፋይናንስ ጫና የሚቀንሱ የተለያዩ አገልግሎቶችን ይዞ በሰፊው ይመጣል” ሲሉ አክለዋል።
አቶ ሰልማን መሀመድ ፣የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ፣የብሔራዊ የነዳጅ የድጋፍ ፕሮጀክት ቢሮ፣ ፕሮጀክት ማኔጀር በበኩላቸው “ካቻ ዲጂታል ፋይናንሻል ሰርቪስ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የነዳጅ ግብይት ስርዓቱን ለማዘመን ያበለጸገውን የነዳጅ ስርጭት መከታተያ (fuel aggregator) የአሰራር ሂደት ተከትሎ እንዲሁም የሚጠበቅበትን አሟልቶ፣ ለህብረተሰቡ የዲጂታል ክፍያ አማራጭ ሆኖ መቅረቡን ገልጸው ካቻ በርካታ የዲጂታል
ፋይናንሻል አገልግሎቶችን የሚሰጥ ተቋም መሆኑን አክለዋል”።
ካቻ በትራንስፖርቱ ዘርፍለተሰማሩ የሜትር ታክሲ (Ride Hailing) ፣ ባለ ሶስት እግር አሽከርካሪዎችን ያማከለ የአጭር ጊዜ የዲጂታል ፋይናንስ እንደሚያቀርብ ይታወቃል።
በተጨማሪም ማንኛውም የተሽከርካሪ ባለቤቶች ከየትናውም ቦታ ሆነው በእጅ ስልካቸው ለመኪናቸው መድህን ዋስትና በዲጂታልየፋይናስ አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን አማራጭ ፈጥሯል። አሽከርካሪዎች የነዳጅ ክፍያን በዲጂታል ፋይናንስ አቅርቦት የሚክፍሉበትን አማራጭ በቅርቡ እንደሚያቀርብ እንዲሁም ተደራሽነቱን በሀገሪቱ ባሉ የነዳጅ ማድያዎች እንደሚያስፋፋ በምርቃቱ ላይ ተገልጿል ።
ካቻ ዲጂታልፋይናንሺያል ሰርቪስ አ.ማ ማህበረሰባችንን አካታች የሚያደርጉ የዲጂታል ፋይናንሻል አገልግሎቶችን ብሔራዊ ባንክን ባወጣው ህግና ደንብ መሰረት ከሌሎች አጋር የፋይናንስ ተቋማት ማለትም ከባንኮች፤ የመድህን ድርጅቶች(ኢንሹራንስ)፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ፤ ከብድርና ቁጠባ ተቋማት እና አለማቀፍ የሃዋላ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በመሆን የተለያዩ አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ ኩባንያ ነው።
በተለይም የማይክሮ ፋይናንስ እና የብድርናቁጠባ ተቋማትን በዲጂታል ሲስተም በማስተሳሰር እና በማዘመን ከዚህ በፊት በውስን ቅርንጫፎች ብቻ ተወስነው የነበሩትን በጊዜ እና ቦታ ሳይገደቡ በቀላሉ በUSSD እና Mobile App ለደንበኞቻቸው ተደራሽ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡