ኢትዮጵያ የውጭ ዜጎች የቋሚ ንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚፈቅድ ህግ አዘጋጀች

የውጭ ዜጎች በኢትዮጵያ ውስጥ የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤት ወይም የመሬት ባለይዞታ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው የአዋጅ ረቂቅ ተዘጋጅቷል፡፡

አዋጁ የተዘጋጀው “የዜጎችን የመሬት ይዞታ የማግኘትና የመጠቀም መብት በማያጣብብ መልኩ” እንደሆነ ተገልጿል።

የውጭ ዜጎች ካፒታላቸውን “በኢትዮጵያ ስራ ላይ እንዲያውሉ ለማበረታታት” የታለመ ነው የተባለለት ይህን የህግ ረቂቅ ለፓርላማ የመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የአዋጅ ረቂቁን ጨምሮ በስድስት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ዜጎች የመሬት እና የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ህጋዊ አሰራር እንዲዘረጋ ከተደረገባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ ለኢትዮጵያውያን “የስራ ዕድል ለመፍጠር ትልቅ ጠቀሜታ” ያለው በመሆኑ እንደሆነ ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

በኢትዮጵያ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና አቅርቦት “ሚዛን ለማስጠበቅ” አዋጁ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል።

የአዋጅ ረቂቁ የቤት ልማት እና ተደራሽነትን “ይበልጥ ለማነቃቃት” የሚያስችል መሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ይህ የህግ ረቂቅ የተላለፈለት የተወካዮች ምክር ቤት፤ የውጭ ባለሃብቶች በሪል ስቴት ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችል ሌላ አዋጅ ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ማጽደቁ አይዘነጋም።

“የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይት እና ግመታ” የሚል ስያሜ ያለው ይህን አዋጅ ለማብራራት የቀረበ ሰነድ፤ የውጭ ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ የተፈለገበትን ምክንያት አብራርቶ ነበር።

በኢትዮጵያ ያለው የቤት እጥረት “አጠቃላይ ሀገራዊ የዕድገት ሂደትን ሊያናጋ በሚችል ደረጃ የሰፋ ስለሆነ፤ ሀገራዊ የካፒታል አቅምም ዝቅተኛ በመሆኑ እና የቴክኖሎጂ እጥረትም ስላለ፤ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል በሚያግዝ መልኩና የውጭ ምንዛሬ አቅም በማይፈትን ሁኔታ በቤት ልማቱ የውጭ ባለሃብትን ማስገባት አስፈላጊ ሆኗል” ሲል ማብራሪያው አትቷል።

የውጭ ሀገር ሰዎች በኢትዮጵያ የንብረት ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ህግ እየተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸው ከአንድ ዓመት በፊት ነው። በመጋቢት 2016 ዓ.ም. በነበረ አንድ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ይህን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነበሩ።

ኢትዮጵያ ከአዲሱ አዋጅ መዘጋጀት በፊት፤ የውጭ ዜጎች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ከሌላቸው በቀር የንብረት ባለቤት እንዳይሆኑ የሚከለክል አሰራር ስትከተል ቆይታለች።

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *