ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀ ድርድር በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ማዕቀፍ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥን ለማቀላጠፍ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚህም መሰረት በሞያሌ ድንበር ላይ ለሚደረጉ የሸቀጦች ንግድ የመጀመሪያ ጣሪያ 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እንዲሆን ተወስኗል።
በሞምባሳ የተጠናቀቀው ይህ ስምምነት የንግድ ሂደቶችን በማቅለል የድንበር ማህበረሰቦችን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ያለመ ነው።
በስምምነቱ የኢትዮጵያ የድንበር ንግድ ዞን ከሞያሌ በ50 ኪሎ ሜትር እንዲሁም የኬንያ ደግሞ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚወሰን ነው።
ነጋዴዎችም በጋራ በተስማሙበት የምርት ዝርዝር መሰረት እስከ 1 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የንግድ ልውውጥ በወር እስከ አራት ጊዜ ድረስ ማካሄድ ይችላሉ ተብሏል።
ይህ ስምምነት የንግድ ዋጋ ጣሪያዎችን፣ የጉዞ ድግግሞሽን እና የድንበር ንግድ ዞኖችን የመሳሰሉ ጉዳዮችን በመዳሰስ ለሁለት ዓመታት በዘለቀ ድርድር የተገኘ ውጤት ነው ተብሏል።
ኬንያ እና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ንግዳቸውን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ሲሆኑ ባሳለፍነው ነሀሴ ወር ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኛትን የባቡር መስመር በ14 ቢሊዮን ዶላር ልትዘረጋ መሆኑን መግለጿ ይታወሳል፡፡
ኬንያ የምትዘረጋው ይህ ፈጣን የባቡር መስመር በኤሌክትሪክ ይሰራል የተባለ ሲሆን፤ መነሻውን ከህንድ ውቅያኖስ ላሙ ወደብ በማድረግ ኢትዮጵያን እና ደቡብ ሱዳንን እንደሚያገናኝ ብሉምበርግ ዘግቧል።
በዓይነቱ ልዩ ነው የተባለው ይህ የባቡር መስመር በፈረንጆቹ 2025 ሥራ እንደሚጀመር እና 3 ሺሕ ከሎ ሜትር እንደሚረዝም ታውቋል፡፡
የባቡር መስመሩ መነሻውን ከህንድ ውቅያኖስ አድርጎ፣ በኬንያዋ ማዕከላዊ ከተማ ኦሲዮሎን በኩል፣ ናይሮቢን እና አዲስ አበባን በማገናኘት የመጨረሻም መዳረሻውን ደቡብ ሱዳን ጁባ እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡
ይህ ፈጣን የባቡር መስመር “ኢትዮጵያ በአሰብ እና ምጽዋ እንዲሁም ጅቡቲ ወደቦች ላይ ያላትን ጥገኝነት የሚቀንስ ነው” የተባለ ሲሆን፤ ሌሎች በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች እንዳሉትም ተገልጿል፡፡
በዚሁ ፈጣን የባቡር መስመር ዝርጋታ አማካኝነት ደቡብ ሱዳን ኹለተኛ ወደብ እንደሚኖራትም ተመላክቷል።
የባቡር መስመር ዝርጋታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት በሚጀምርበት ወቅት ከላሙ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል፡፡
ኬንያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የላሙ ወደብን ለማልማት እና ለመጠቀም በ2001 ዓ.ም በኬንያ ፕሬዝዳንት፣ ሞ ኪባኪ፣ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እና በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት አማካኝነት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ኬንያ ይህን ፕሮጀክት በማልማት ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን እንዲጠቀሙበት ፍላጎት ያላት ቢሆንም ኢትዮጵያ እስካሁን ፍላጎት እንዳልነበራት ተገልጿል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ኢትዮጵያ ተጨማሪ የገቢ ወጪ ንግድ አማራጭ ወደብ እንዲኖራት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ሲሆን የላሙ ወደብን አንዱ አማራጭ አድርጎ ለመጠቀም መወሰኑ ተገልጿል፡፡
ይህ ተከትሎም ኬንያ ከላሙ ወደብ በሞያሌ አድርጎ አዲስ አበባ የሚደርስ የባቡር መሰረተ ልማት ለመገንባት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡