ጀነራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሆነው ተሾሙ

የትግራይ ጊዝያዊ አስተዳደር ከተመሰረተ በኃላ ላለፉት ሁለት ዓመታት የአቶ ጌታቸው ረዳ ምክትል በመሆንና የሰላምና ፀጥታ ካቢኔ ሲክሬተርያት ሀላፊ ብሎም የትግራይ ጦር አዛዥ በመሆን ሲሰሩ የቆዩት ጀነራል ታደሰ በዛሬው እለት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ሆነው ተሾመዋል።

ጀነራል ታደሰ ቀደም ሲል በህወሓት አቶ ጌታቸውን በመተካት ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ተመርጠው ፌደራል መንግስትም ይህንኑ የህወሓት ምርጫ ተቀብሎት እንደነበር ከዚህ ቀደም ፓርቲው ማስታወቁ አይዘነጋም።

ጄኔራል ታደሰ ወረደ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነትን የተረከቡ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና ሌሎች አካላት በስልጣን ርክክቡ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ጀነራል ታደሰ ወረደ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት፣ መልሶ ማቋቋም፣ በክልሉ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ማድረግ፤ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለሰላም እና ለጸጥታ ጠንቅ የሆኑ ጉልህ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ማድረግ፤ ለዚህም ተገቢውን የቁጥጥር እና የሕግ ማስከበር ሥራ ለመሥራት ቃል ገብተዋል፡፡

እንዲሁም መደበኛ የልማት ሥራዎች፣ መንግሥታዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እንዲሣለጡ ማድረግን ጨምሮ ከሕገ መንግሥታዊ እና ከሕጋዊ ሥርዓት፣ ከሀገር_ሉዓላዊነት እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ያፈነገጡ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎችን አስቆማለሁ ብለዋል፡፡

ክልሉ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግ፤ በክልሉ የሲቪክ እና የፖለቲካ መብቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ እና  የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ ደሞክራሲያዊ ዐውድ እንዲፈጠር ለመሥራትም ቃል ገብተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ሕዝብ፣ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እና የፖለቲካ ተዋንያን በሀገራዊ_የምክክር_ሂደት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና የክልሉ መንግሥታዊ የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን እንቅስቃሴዎች የሀገሪቱን ሕዝቦች ትሥሥር እና መልካም ግንኙነት የሚያጠናከሩ፣ ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚያስከብሩ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በስልጣን ርክክቡ ወቅት ቃል ገብተዋል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ በይፋ በትናንትናው ዕለት ከስልጣን መሰናበታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፉት ሁለት አመታት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን በይፋ አሰናብተዋል፡፡

By New admin

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *